(ኢሳት ዜና–መስከረም 8/2010) በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት እስካሁን ከ50 ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ።
በሁለቱም ክልሎች አካባቢዎች በነበረው ግጭት የሞቱት ሰዎች ልክ በውል ባይታወቅም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ ግን ግምቶች አሉ።
እየተባባሰ በሄደው ግጭት ሳቢያ ሲወዛገቡ የነበሩት የሁለቱ ክልል ፕሬዝዳንቶች በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካኝነት የጋራ መግለጫ እንዲሰጡ ተደርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱ ፕሪዝዳንቶች መግለጫ ከሰጡ በኋላ ውጊያ መካሄዱንና አንድ የጸጥታ ሀይል ተገድሎ ከ 1500 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት የሁለቱም ክልሎች ቃል አቀባዮች ይፋዊ በሆነ መንገድ እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ ሰንብተዋል።
ከኦሮሚያ በኩል የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ሰላማዊ ሰዎችንና ሁለት የወረዳ አመራሮችን መግደሉን ተከትሎ የተባባሰ ግጭት መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።
በሶማሌ በኩል ደግሞ አወዳይ በተባለ አካባቢ 50 የልዩ ፖሊስ አባላት በኦሮሚያ ታጣቂዎች ስለተገደሉ በተሰጠ የአጸፋ ምላሽ ግጭቱ መባባሱ ሲነገር ነበር።
የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው በአካባቢው 50ሺ ሰዎች ሲፈናቀሉና በመቶዎች ሲገደሉ ግን የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ ሳይገባ መቆየቱ ብዙዎችን አስገርሞ ቆይቷል ።
የኋላ ኋላ ግን የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ግጭቱን አስቁሟል ቢባልም ስደቱና መፈናቀሉ እንዲሁም ግድያው አለመቆሙን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸው ቀጥሏል።
እናም ጉዳዩ መባባሱ የሁሉንም ትኩረት በመሳቡና በግጭቱ ሰላማዊ ሰዎች በእጅጉ መጎዳታቸው የክልሎቹን ባለስልጣናት የቃላት እንካ ሰላንትያ እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል።
ይህም በፌደራሉ መንግስት ትእዛዝ ሊሆን እንደሚችል ታዛቢዎች ይናገራሉ።
አሁን ደግሞ የኦሮሚያው ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳና የሶማሌው ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሙሀመድ ኦማር በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል የጋራ መግለጫ ለመስጠት ተገደዋል።
ሁለቱም ባለስልጣናት እኛ እናልፋለን ፥ ሕዝብ ግን ዘላለማዊ ነው፥ ስለዚህም ጥፋቱ ያለው ከእኛው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መግለጫ ከሰጡ በኋላ ወጊያ መካሄዱንና አንድ የጸጥታ ሀይል ተገድሎ ከ 1500 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።
በኦሮሚያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በጭናቀሰን እንዲሁም በባቢሌ አካባቢ ውጊያ ተካሂዷል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የሀሮሬሳ ቀበሌ የጸጥታ ሀላፊ መገደላቸውም ተነግሯል።
ከጅጅጋ ወደ ሀረር ተፈናቃዮችን ሲያመላለሰ የነበር አይሱዚ መኪናም ተገልብጦ በርካታ ሰዎች ሲሞቱ በዚሁ ሳብያ የቆሰሉ ሰዎችም ወደ ሀረር ሆስፒታል ተወስደዋል፤
ሪፖ/ምስ/ኢተ