ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2009)
የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ዕልባት አለማግኘቱንና በሁለቱ ወገኖች ከ400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ ገለጸ።
ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ በፌዴራል መንግስት ድጋፍ ይደረግላቸዋል የተባሉ የሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ አባላት 15 በሚሆኑ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት በመውሰድ ላይ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ይኸው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ያስታወቀው ሊጉ ከአራት ቀን በፊት በባሌ ሳወና ወረዳ ቀሌሳ ተብሎ በሚጠራ የደቡባዊ ኦሮሚያ አካባቢ የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች በወሰዱት ዕርምጃ በትንሹ 19 የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸውንና 13ቱ መጎዳታቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል በወሰዱት ዕርምጃ ከልዩ ታጣቂ አባላት በኩል 35 መሞታቸውን እንዲሁም ወደ 50 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሊጉ የአካባቢውን ነዋሪዎችን መረጃ ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በአጠቃላይ ካለፈው ስድስት ወር ጀምሮ በ15 ወረዳዎች ውስጥ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት ከ200 በላይ የኦሮሞ ተወላጆች መሞታቸውን እንዲሁም ወደ 150 የሚጠጉት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ አመልክቷል።
የአካባቢው ተወላጆች እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ለመከላከል በወሰዱት ዕርምጃ 260 የሚሆኑ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ እና የፌዴራል የጸጥታ አባላት መሞታቸውን፣ በርካቶች መጎዳታቸውን ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃትና ወረራ ዝም ብለው እየተመለከቱት እንደሆነ የሚገልጸው ሊጉ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ንብረታቸው እየተወሰደና ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀውም ታፍነው እንደተወሰዱ ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
የፌዴራል ባለስልጣናት በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ በቅርቡ ቢያረጋግጡም የሟቾች ቁጥርን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች በጉዳዩ ዙሪያ ባለፈው ወር ባወጡት መግለጫ የመንግስት ታጣቂዎች የኦሮሚያ ክልል ይዞታን እና ሃብትን በሃይል ለመናድ ጥረት እያደረጉ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በቅርቡ ከጋምቤላ ክልል የተላኩ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በምዕራብ ወለጋ በቀለምና ያቲ ዞኖች ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን በመውሰዱ በርካታ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው እንዳፈናቀሉም ሊጉ ለአለም አቀፍ አካላት ባሰራጨው ሪፖርቱ አመልክቷል።