በእግር ኳስ ግጥሚያው አምባሳደሮቹ አለመጫዎታቸው እያነጋገረ ነው

መጋቢት ፳፬ (ሃይ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የህዳሴውን ግድብ ግንባታ አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መመቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የውጪ አገር ዲፕሎማቶች ከኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት ጋር የእግር ኳስ ግጥሚያ እንደሚያደርጉ ኢቲቪና ሌሎች የመንግስት ብዙሀን መገናኛ ሲዘግቡ ቢሰነብቱም፤አምባሳደሮቹ አለመጫዎታቸው እያነጋገረ ነው።

ኢቲቪ ከቀናት በፊት ፤የመንግስት ባለሥልጣናት ከውጪ አምባሳደሮች ጋር የ እግር ኳስ ጨዋታ እንደሚያካሂዱ በማሣወቅና   የአምባሰደሮቹን ቡድን ለመግጠም ባለሥልጣናቱ  ስላደረጉት ዝግጁነት ቃለ-ምልልስ በማድረግ ነበር የዘገባው

ከዚህም ባሻገር የ ህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ አምባሳደሮቹ  ከመንግስት ባለሥልጣናት ጋር ኳስ በመጫዎት ለ አባይ ግድብ ያላቸውን ድጋፍ ያሳያሉ በማለት መናገራቸው አይዘነጋም።

ይሁንና  ምክንያቱ  ባልተገለጸ ሁኔታ አምባሳደሮቹ ባለመጫዎታቸው፤የእግር ኳስ ጨዋታው በባለሥልጣናቱና  የአቶ ሠራዊት ፍቅሬ ቡድን አባላት በሆኑ አርቲስቶች መካከል ተካሂዷል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፤የአባይ ጉዳይ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪቃ ቀንድ ዋነኛ ትኩሳት እየሆነ በመጣበት ጊዜ የውጪ አምባሳደሮች ለዓባይ ግድብ ተብሎ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ኳስ አለመጫዎታቸው እንደማይገርም በመጥቀስ፤ “ይገርም የነበረው ቢጫዎቱ ነበር”ብለዋል።

“ቀድሞውኑም፤ አምባሳደሮቹ ኳስ በመጫዎት ለዓባይ ግድብ ያላቸውን ድጋፍ ያሳያሉ” የተባለው ነገር በደመ-ነፍስ ወይም በግንዛቤ እጥረት  የተነገረ ይመስለኛል”ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ፤   ከዘጠኝ በላይ የራስጌና የግርጌ ተፋሰስ አገሮች  ዓይናቸውን ባፈጠጡበት በዓባይ ወንዝ  ጉዳይ ዲፕሎማቶቹ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚራመዱ ሊጤን ይገባል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በጨዋታው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እንደሚሳተፉ ቢነገርም፤ ከአርቲስቶቹ ጋር በተደረገው ግጥሚያ የተሳተፉት ግን  ከጥቂቶች በስተቀር ብዙም የሚታወቁ አይደሉም።

ከተቻዎቱት ባለሥልጣናት ሻል ባለ ደረጃ የሚታወቁት የፍትህ ሚኒስትሩ ብርሀነ ሀይሉ፣የ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ሥራ አስሊያጅ ምህረት ደበበ እና አባዱላ ገመዳ ናቸው።

ተቃዋሚ ፓርቲ በሌለበት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ተብለው የተቀመጡት አቶ አባዱላም የሚታወቁት ቀደም ሲል በነበረው እንጂ አሀን በያዙት ሥልጣን አይደለም።

“እነ መለስንና እነበረከትን የመሣሰሉት ዋና ዋና ባለሥልጣናት ለምንድነው ያልተጫዎቱት?” የሚል ጥያቄ ለአንዱ ወዳጁ አንስቶለት እንደነበር ያወሳው አቤ ቶክቻው፦ተጠያቂውም መልሶ፦”እነሱ በሰው እንጂ፤ በኳስ መጫዎት አይችሉም” እንዳለው በማስታወሻው ላይ አስፍሯል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide