ጥቅምት ፲፰ (አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቱሪዝም አስጎብኚነት የተሰማሩ የእንግሊዝ ድርጅቶች ለክብረ በዓላት እና ለጉብኝት ወደ ታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞዎች ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።
ድርጅቶቹ የጉዞ እገዳቸውን አስመልክቶ በምክንያትነት ያቀረቡት ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን ሕዝባዊ አመጽ አድማሱን በማስፋቱ የደኅንነት ስጋት በአገርቱ በመፈጠሩ ነው። የእንግሊዝ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኮክስ፣ ሳጋ እና ኪንግ የተባሉ ታዋቂዎቹ አስጎብኚ ድርጅቶች በጋራ ጉዟቸውን ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውንና ለደንበኞቻቸው ቅድመ ክፍያውን እንደሚመልሱ ወይም ተለዋጭ አማራጮችን እናቀርባለን ብለዋል።
“በኢትዮጵያ ለስድስት ተከታታይ ወራት የሚዘልቀው አፋኙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በቅርቡ ከ1 ሽህ 600 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ ታስረዋል። በታጣቂዎች እና በሰላማዊ ሰልፈኞች መሃከል ግጭቶች ተከስተዋል። በጸጥታ አስከባሪዎች ሰላማዊ ዜጎች ተገለዋል። በእሬቻ በዓል ላይ የመንግስት ወታደሮች አስለቃሽ ጋዝ መተኮሳቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን እና በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አሁንም ቀጣይ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሊቀጥሉ ይችላሉ” ሲል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
በሕዝባዊ አድማው ምክንያት መንገዶች ዝግ መሆናቸው ከደኅንነት ስጋት ጋር ተደምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ማንኛቸውም የቱሪዝም ጉብኝቶች በያዝነው ዓመት መሰረዛቸውን አስጎብኚ ድርጅቶችን ጠቅሶ ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል።
በምስራቅ አፍሪካ ተመራማሪ የሆኑት ኤማ ጎርዶን በበኩላቸው የመሬት ቅርምቱን የተቃወሙ ዜጎች በመስረተ ልማቶች እና በውጭ ኢንቨተሮች ንብረት ላይ ውድመት አድርሰዋል። ይህም የመንግስት አቅም እየተዳከመ ተቀባይነቱ እየቀነሰ መምጣቱን እና ሕጋዊነቱ አጠያያቂ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል ብለዋል። ሕዝባዊ ተቃውሞው የሚያሳየው ነገር ቢኖር ገዥው ፓርቲ እና አጋር ድርጅቶቹ ቆም ብለው በቀናነት የምርጫ ተሃድሶዎችን ጨምሮ ከተቃዋሚዎች ጋር ለድርድር ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል። ይህም ወደ ትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ይወስዳቸዋል። በብሔር ላይ የተመሰረተው የፌደራል መዋቅር እና የጸጥታ ሃሎች ሚና በድጋሜ መከለስ ይገባዋል። የግል ባለሃብቶች መዋእለ ንዋያቸውን ከማፍሰሳቸው አስቀድመው የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ሊያጤኑት ይገባል ሲሉ ተመራማሪዋ መምከራቸውን ጀስት ስታይል ዘግቧል።