ሐምሌ ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ በሴትነቷ ጥቃት እንደተፈጸመባት በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ያደረገችው በሰሜን ጎንደር ተካሂዶ የነበረውን ህዝባዊ አመጽ በማስተባበር በተከሰሰችው ንግስት ይርጋ እና ሌሎች ተከሳሾች ላይ ሊቀርቡ የነበሩት የአቃቢ ህግ ምስክሮች ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ፌደራል ፖሊስ የምስክሮችን አድራሻ አለማግኘቱን በመናገር ሌላ ቀጠሮ ጠይቋል።
የተከሳሾች ጠበቃ አቃቢ ህግ ለ5ኛ ጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጠው ገልጾ፣ ሰ”ዎች ከጎንደር መጥተው ሲመሰክሩ አዲስ አበባ ያሉትን አግኝቶ ለማስመስከር ሊከብድ አይችልም፣ በተደጋጋሚ ተቀጥሮ ተሰጥቶ የሚመጡትን ምስክሮች አልፈልጋቸውም ብሎአል። የፖሊስ ምክንያት አሳማኝ ባለመሆኑ ደንበኞቼ እየተጉላሉብኝ ነው” ሲል አክሏል።
ወ/ት ንግስት “ እኛ ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ መከራ አሳልፈናል። መቆም እስኪያቅተን ተደብድበናል። ምንም ማስረጃ ሊገንብን አልቻለም። ቤተሰብ ማግኘት አልቻልም። እኔ በሰው ሃገር ተንከራትቼ ነበር ቤተሰብ የማስተዳድረው፣ ደካማ እናት አለችኝ። አሁንም የሚያስተዳድራት የለም። አቃቢ ህግ ምስክሮች ቢኖሩት ኖሮ እስካሁን አቅርቦ ያሰማ ነበር። እኛ በምቾት አይደለም ያለነው።” ስትል በምሬት ተናግራለች።
ወ/ት ንግስት በቤተሰብ የምትጠየቀው ካስመዘገበቻቸው ሰዎች ውጭ ሊጠይቋት እንደማይችሉ፣ እንዲሁም የመጠየቂያ ጊዜው ከ6 ሰአት እስከ 6 ሰአት ተኩል ብቻ በመሆኑ፣ ከ750 ኪ/ሜትሮች በላይ ተጉዘው የሚመጡ ጠየቂዎቿ እየተንከራተቱ መሆኑን ገልጻለች።
ፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ተጨማሪ ቀጠሮ ይሰጠው አይሰጠው በሚለው ላይ ለመወሰን ለነገ ረቡዕ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በሌላ በኩል ከዋልድባ ገዳም ታስረው የሽብር ክስ የቀረበባቸው ሶስት መነኮሳት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ጥንታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳም የሆነው ታሪካዊው የዋልድባ ገዳምን ለስኳር ፋብሪካ ለማድረግ በሚል ኢፍትሃዊ የመሬት ቅርምትን የተቃወሙ መነኮሳት ሃምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸው ተሰምቷል።
የገዳሙ መነኮሳት አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነ ማርያም ካሣዬ እና አባ ገብረሥላሴ ወ/ሃይማኖት ገ/መድኅን ከግንቦት ሰባት የሽብርተኛ ቡድን ጋር ተገናኝተዋል፣ ሁከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ ጥረት አርገዋል፣ መንግሥትን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል ሲል አቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል። መነኮሳቱ ይለብሱት የነበረውን ሃይማኖታዊ አልባሳት በማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪዎች እንዲያወልቁ እና የእስር ቤት መለያ ልብስ እንዲለብሱ ተገደው ነበር። በዛሬው ችሎት ግን ሃይማኖታዊ ልብሳቸውን ለብሰው ቀርበዋል።
ለ5 ወራት ያክል በእስር ላይ ሆነው ስቃይ የሚደረስባቸው መነኮሳቱ አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ክስ እንዳስገረማቸውና በምንም የሽብር ተግባር አለመሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ ሃምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል።