በእነዋሬ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች ከአካባቢያቸው  ከሚዘረፈው  ማዕድን ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ተናገሩ፡፡

ጥቅምት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በሰሜን ሸዋ ዞን ከእነዋሪ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የወረዳዋ ሃብት ከሆኑ ተራራዎች ለሲሚንቶ አገልግሎት ሊውል የሚችል ማዕድን በየቀኑ እየተጫነ መጓጓዙ አግባብ አለመሆኑን በእነዋሬ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በየቀኑ የሚመላለሱት ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች የከተማዋን መንገድ በማፈራረስ ላይ መሆናቸውንም የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው  የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ ሊሆን የሚገባው የአካባቢው ማህበረሰብ መሆን ሲገባው ማዕድኑን ክልል አቋርጦ በመጫን ለሌሎች አካባቢ ነዋሪዎች ጥቅም ብቻ እንዲውል መድረጉ እንዳስከፋቸው በከተማዋ የሚኖሩ ወጣቶች ተናግረው፣ በአካባቢያችን በሚገኝ ሃብት በመጠቀም ድህነትን መዋጋት ባለመቻላችው ሁለተኛ ዜጋ እንደሆኑ እንደሚሰማቸው ለዘጋቢያችን አስረድተዋል ፡፡

የሲሚንቶ ማዕድኑ በወረዳዋ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ በአካባቢው ፋብሪካ በመክፈት በርካታ ስራ አጦችን ሊያግዝ የሚያስችለውን ዕድል በማጠፍ ፋብሪካው ወደ ሌላ አካባቢ መወሰዱ አግባብ አለመሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አሰራሩ ትክክል አለመሆኑን በመናገር የተቃወሙ ወጣቶችን በማሰር ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ እንዳደረሱባቸው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ህዝብ በበርካታ ነገሮች እየተጎዳ መሆኑ የወረዳዋም ጉዳት እንደሆነ እምነታቸውን የገለጹት የእነዋሬ ከተማ ወጣቶችና ነዋሪዎች ፣ በክልሉ ስር ይገኙ የነበሩትን መሬቶች ከመውሰድ አልፎ በክልሉ የሚገኙ  ማዕድናትን  በመዝረፍ የአንድ ብሄር ተወላጆች ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ፍትሃዊ አለመሆኑ በቁጭት ተናግረዋል፡፡

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳዋ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የወረዳውን ማዕድን ለማመላለስ በቀን ከሃያ የማያንሱ የ”ሲኖ ትራክ” ገልባጭ የጭነት መኪናዎች እንደሚመላለሱ ገልጸው፤በከተማዋ የተሰራው ብቸኛ የአስፋልት መንገድ በመጎዳቱ ወደ ጠጠር መንገድነት እየተቀየረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አመራሮቹ አክለው እንደተናገሩት የጭነት መኪኖቹ በእያንዳንዱ ዙር  ለከተማዋ ልማት በሚል የሚከፍሉት አነስተኛ ክፍያ ቢኖርም መንገዱ ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር ለጥገና እንኳን እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡የጭነት መኪኖቹ አቅጣጫ ቀይረው ከአስፋልቱ መንገድ ውጭ እንዲጓዙ ለማድረግ የተሞከረውን ሙከራ የበላይ አመራሮች ባደረሱት ጫና ማስከበር አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የወጣቶች ጥያቄ  አግባብነት ያለው መሆኑን የሚያምኑት አመራሮች፤ በከተማዋ የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማሰማራት ወረዳዋ ምንም ዓይነት የፋብሪካም ሆነ ሌሎች የስራ ዕድሎች ለማመቻቸት የሚያስችል የበጀት አቅም እንደሌላት ገልጸዋል፡፡  ወጣቶች በየጊዜው በሚደረጉ ህዝባዊ ስብሰባዎች ሁልጊዜም አመራሩን  ሲያማረሩ መስማታቸውን የወረዳዋ  ሃላፊዎች ተናግረው ጉዳዩን ወደ በላይ አመራሮች ሲያቀርቡም በቂ ምላሽ እንደማይሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎችና ወጣቶች በዚህ የማዕድን ዘረፋ ዙሪያ ያላቸውን አቋም በማጠናከር ወረዳዋን ከምዝበራ ሊያድኗት እንደሚችሉ የሚናገሩት የወረዳዋ አመራች ፣ ነዋሪው በግልጽ በመቃዎም በሁሉም አመራር ላይ  የተጠናከረ የተቃውሞ ድምጹን በማሰማት መብቱን ሊያስከብር የሚያስችል ጊዜ ላይ መሆኑ ሊያውቅ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ወቅቱ ሁሉም ህዝባዊ ጥቅሙን እየጠየቀ ያለበት ጊዜ በመሆኑ የወረዳዋ ስራ አጥ ወጣቶችም ሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረታቸው ሲዘረፍ በዝምታ መመልከት እንደሌለልባቸው አመራሮቹ ምክራቸውን ለግሰዋል።