ኢሳት (መስከረም 2 ፥ 2009)
በአዲስ አበባ ስታዲየም እና ዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ሰኞ የኢድ አልድሃ በዓልን ለማክበር የተሰባሰቡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በእስር ላይ የሚገኙ ሁሉም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ በመጠየቅ የተቃውሞ ጥያቄን አቀረቡ።
የቀይ ቀለም ምልክትን የያዘ ወረቀት በመያዝ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የበዓሉ ታዳሚዎች፣ መንግስት ለእስር የዳረጋቸውን ሌሎች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ አሳስበዋል።
የሙስሊሙን ትግል በማስተባበር ላይ የሚገኘው ድምጻችን ይሰማ በበኩሉ፣ ሁሉም የኮሚቴ አባላት እስኪፈቱ ድረስ የተጀመረው ግፊትና ተቃውሞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሰኞ የበዓል አካባበርን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
መንግስት ለተወሰኑ ለሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ምህረትን አድርጌዋለሁ ማለት ባለፈው ቅዳሜ ወሰ ስድስት የሚጠጉ አባላትን ከአመት በፊት እስር በኋላ መፍታቱ ይታወሳል።
ይሁንና አሁንም ድረስ ሌሎች የኮሚቴ አባላት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ለኢድ አልሃ በዓል አከባበር በመዲናይቱ አዲስ አበባ የተሰባሰቡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት እንዲፈቱ ሲሉ የከተማዋ አስተዳደር ባለስልጣናት በተገኙበት ስፍራ መጠየቃቸው ታውቋል።
መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል ሲሉ የነበሩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከአራት አመት በፊት ጀምሮ የመንግስትን ድርጊት በመቃወም የተለያዩ የተቃውሞ ትዕይንቶችን ሲያካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
“በአንድ የክስ መዝገብ የታሰሩ የትግል አጋሮቻቸው አለመፈታት ደስታቸውን ግድሎ፣ ዕረፍታቸውንም ያልተረጋጋ ያደርገዋል” ሲሉ ድምጻችን ይሰማ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ሁሉም የኮሚቴው አባላት እስከሚፈቱ ድረስም ሲያካሄዱ የቆዩ ትግሎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሙስሊሙ ማህበረሰብን ትግል በማስተባበር ላይ የሚገኘው አካል አክሎ አስታውቋል።