ነሃሴ ፳፯(ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሃብታሙ አያሌው፣ የድርጅቱ ም/ል የድርጅት ጉዳይ ሃለፊ ዳንኤል ሽበሺ፣
እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት/ምክትል ሰብሳቢ የሺዋስ አሰፋ ከሰአት በሁዋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ቢሆንም፣ ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ
በሚል የጊዜ ቀጠሮ በመጠየቁ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተሉት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ፖሊስ እስካሁን የተሰጠውን የጊዜ ቀጠሮ በአግባቡ ስላልተጠቀመ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት አይገባም
በማለት ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮውን ከመፍቀድ አልታቀበም።
እስረኞቹ ከቤተሰብ ውጭ ማንም እንዳይጠይቃቸው መከልከሉ አግባብ አለመሆኑን አቶ ተማም ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱም እስረኞቹ መብታቸው ተከብሮ በሌሎች ሰዎችም
ይጠየቁ የሚል ትእዛዝ አስተላልፏል። ጠበቃ ተማም ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ የሚሰጠው ትእዛዝ እየተፈጸመ ባለመሆኑ፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ መሆናቸውን
እንዲከታተል ጠይቀዋል። ችሎቱን ለመከታተል የእስረኞች ቤተሰቦች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና አባላት እንዲሁም ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት መጪውን ምርጫ አስታኮ የተቃዋሚ ድርጅት አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ማሰሩን ተቃውሞአል።
ሰሞኑን የህብረቱ ተወካዮች ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይትም ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቀዋል።