መስከረም ፳፮ (ኅያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቡድኑ ነገ ሃሙስ ክሳቸው ለ37ተኛ ጊዜ በፍርድ ቤት የሚታየውና በመፃፋቸው ብቻ በአሸባሪነት ክስ ተወንጅለው በእስር ላይ የሚገኙት አራቱ የዞን 9 ጦማሪያን ቡድን አባላት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ክሳቸው ተቋርጦ በነፃ እንዲለቀቁ ሲል አሳስቧል።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች አጥናፍ ብርሃነ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣አቤል ዋበላ እና ናትናኤል ፈለቀ እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር በ2009 በወጣው የሽብርተኝነት ሕግ መሰረት ከ10 ዓመት እስከ 15 ዓመት ሊያሳስራቸው የሚችል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ ክሱም ከውጭ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራትና ገንዘብ በመቀበል በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ረብሻ መፍጠር የሚሉ ናቸው።
ከጋዜጠኞች ጋር በተመሳሳይ ክስ ተወንጅለው አብረው ታስረው ከነበሩት ውስጥ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ሁለቱ ጦማሪያንና አራት ጋዜጠኞችን ፍትሕ ሚንስቴር ህጋዊ የሆነ መረጃ ሳያቀርብ ክሱን በማንሳት በነፃ አሰናብቷቸዋል።
ፍትሕ ሚንስቴር ክሳቸው አንስቶ በነጻ ማሰናበቱ በወቅቱ በበጎ ጎኑ የታየ ቢሆንም ከፍርድ በፊት ውሳኔው አስቀድሞ መደረጉ ግን ለፍትሕ ሚኒስቴር ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል ታዛቢዎች ጠቁመዋል።ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ከተለቀቁት በነፃ ከተለቀቁት አራቱ ጦማሪያን የተለየ የፈፀሙት ምንም ዓይነት አዲስ ወንጀል ስለሌለ ክሳቸው ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ተነስቶ በነጻ እንዲለቀቁ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
እኛ ለፍርድ ቤቱና ለባለስልጣናቱ የምናሳስባቸው ነገር ቢኖር በዞን 9 ጦማሪያ ጉዳይ ላይ ፍትሃዊና ግልፅ መሆን ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የአፍሪካ ዴስክ ኃላፊ ክሊያ ካህን ሲርበር ተናግረዋል። በእነሱ ላይ ምንም ዓይነት ተጨባጭ የሆነ መረጃ ስለሌለ በአንድ ላይ የሁሉም ክስ ተቋርጦ በነፃ መለቀቅ አለባቸው ሲሉ አክለዋል።
ስለሚያገባን እንጦምራለን በሚል መሪ ቃል በሰብዓዊ መብትና በፍትሕ ጉዳይ ላይ የሚፅፉት የዞን 9 አባላት ፣ በ2012 ዓ.ም የተመሰረቱ ሲሆን በዛው ዓመት ላይ ድረገፃቸው አገር ውስጥ እንዳይነበብ መከልከሉ ይታወሳል።
በ2009 ዓ.ም የወጣው የአሸባሪነት ሕግ በሕጋዊነት ሽፋን በነፃነት የመጻፍን ሕጋዊ መብት ለማፈን መሆኑን ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ጠቅሶ ይህ ሕግ ከወጣ በኋላ ብዙ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና ከአገር መሰደዳቸውን አውስቷል። ኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግን በማፈን ከ180 አገራት ውስጥ 142 ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ዓለማቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በጥናታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙትን የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ከእስር ለማስፈታት ተንቀሳቅሰዋል፤ ለአመፅ የሚጋብዙ በራሪ ወረቀቶችን በየመንደሩ በትነዋል፤ በተለያዩ መስጂዶች ሕዝበ-ሙስሊሙ ለአመፅ እንዲነሳሳ ቀስቅሰዋል፤ እና ኮሚቴውን ለመተካት ተንቀሳቅሰዋል በሚል በእነኤሊያስ ከድር መዝገብ ስር የተከሰሱ 16 ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ለመስጠት መቀጠሩን ሰንደቅ ዘገበ።
ተከሳሾች ኤሊያስ ከድር፣ ሙባረክ ከድር፣ ቶፊቅ መሀመድ፣ ፌይሰል አርጋው፣ አብዱልመጂድ አብዱልከሪም፣ እስማኤል ሙስጠፋ፣ ሬድዋን አብደላ፣ አንዋር ሱልጣን፣ አብዱላዚዝ ፈቱዲን፣ ጃፋር ዲጋ፣ ፉሩቅ ሰኢድ፣ መሪማ ሃያት፣ መሀመድ አሊ፣ መሀመድ አይለየን፣ አክበር ሰልማን እና ሙአዝ ሙደሲርናቸው። ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለህዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።