በእስር ላይ የሚገኙት የበለሳ ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለወራት ፍርድ ቤት አልቀረቡም

ሐምሌ ፲፸ (አስራሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አቶ ፈንታሁን ታደሰና ሌሎች 6 እስረኞች ለ5 ወራት ያህል ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
በፖሊስ የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. የታሰሩት እነ አቶ ፈንታሁን በወቅቱ የጉሃላ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ወስዷቸው የነበር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ”እኛ ይህን ጉዳይ አናይም! ከፈለጋችሁ ወደ ዞን ፍርድ ቤት ወስዳችሁ አሳዩ” ብሎ መልሷቸዋል፡፡ፖሊስ እስረኞቹን ወደ እስር ቤት ከመለሳቸው በኋላ እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና መርማሪዎችም ጉዳያቸውን እንደማይከታተሉ ጋዜጣው ዘግቧል።
ከሌሎች እስረኞች ተለይተው በአንድ ክፍል መታሰራቸውን የገለጸው ጋዜጣው፣ ከ7ቱ እስረኞች ውስጥ ሁለቱ ፖሊሶች ናቸው፡፡ የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ታስረው እስካሁን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በጉሃላ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት እስረኞች ፈንታሁን ታደሰ የሰማያዊ ፓርቲ አባል፣ ፖሊስ አማኑኤል አደራ፣ ፖሊስ ዋሲሁን ጌትነት ፣ ሾፌር ስጦታው ምስጋናው ፣ ጌታቸው ተኮላ ፣ ሙሉጌታ ምህረትና አደራ መብራቱ ናቸው።