በእስር ላይ በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ አሰቃቂ ድበደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ታወቀ

ሐምሌ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የኢሳት የፖሊስ ምንጮች እንደተናገሩት ባለፈው ሳምንት በሙስሊሙና በመንግስት መካካል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በተለያዩ እስርቤቶች በሚገኙ አማንያንና አመራሮች ላይ የሚፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት እየጨመረ መምጣቱ ፣ አንዳንድ እስረኞች ስቃዩን መቋቋም ተስኖአቸው መንግስት የሚፈልገውን ሁሉ እንዳሉና ከስቃይ ለመገላገል ችለዋል።

ሰውነታቸው ተገልብጦ የውስጥ እግራቸው የተገረፈ፣ ብልታቸው የተቀጠቀጠ፣ ጭናቸው መሀል ላይ መቆንጠጫ ብረት  የገባላቸው፣ እጃቸው የፊጥኝ ለሁዋሊት ታስሮ ከ48 ሰአት በላይ የቆዩ፣ ስለታማ በሆኑ ደንጋዮች ላይ እንዲራመዱ የተደረጉ ሙስሊሞች አሉ።

ብዙዎቹ በአመራሮች ላይ መስክረው እንዲወጡ፣ እንዲሁም አንዳንዶች የግንቦት7 አባላት ነን ብለው እንዲናገሩ ግፊት ሲደረግባቸው ነበር። አንዳንድ እስረኞች ስቃዩ ቢበዛባቸውም ” አላህ ክበር” በማለት ጩሀት ከማሰማት ውጭ፣ የደብዳቢዎችን ፍላጎት አላሟሉም።

እጅግ አስገራሚ የነበረው ይላሉ የፖሊስ ምንጮች ድብደባውን የሚፈጽሙት ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎች ሲሆኑ፣ የሌሎች ብሄር ተወላጆችና ሙስሊም ፖሊሶች ከማሰቃያ ቦታዎች እንዲርቁ ተደርጓል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ  የድምጻችን ይሰማ አመራሮች አፈቀላጤ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ጋዜጠኛ አክመል ነጋሽና ይሽሀቅ እሸቱ ቤታቸው በፌደራል ፖሊስ እየተበረበረ ባለበት ወቅት በማምለጣቸው የአክመል ነጋሽ እናት በቁጥጥር ስር ውለዋል። እስረኛው እጁን ካልሰጠ እንደማይለቀቁ፣ ፖሊሶች ለቤተሰቦቻቸው መግለጻቸው ታውቋል።

በሌላ በኩልም በሙስሊሞች ጉዳይ በኢህአዴግን መካከል ክፍፍል መፍጠሩን ሰንደቅ ዘግቧል።

ሰንደቅ ጋዜጣ ፦ “አዲስ ራዕይ “ የተሰኘውን እና የ ኢህአዴግ አመራሮች  በጽሁፍ የሚሳተፉበትን  የንድፈ-ሀሳብ መጽሔት በመጥቀስ እንደዘገበው፤ኢህአዴግ በሕዝበ ሙስሊሙ እና በመስጂዱ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በመረዳት ረገድ በአመራሩና በአባላቶቹ ዘንድ ክፍተት እንደነበረ በይፋ አምኗል።

ይህ የግንባሩ መጽሔት በሰኔ ወር  እትሙ ላይ ፤ “… የራሳቸው የተለየ አጀንዳና አቋም ያላቸው ኃይሎች በኤሌክትሮኒክስና በሕትመት ሚዲያ፣ በአጫጭር የስልክ መልዕክቶች እንዲሁም በበራሪ ወረቀቶችና በሰው ለሰው ግንኙነት በበተኑት የታሰበበትና በቅንጅት በተፈፀመ ዘመቻ ፤ አባሎቻችንን ጨምሮ በበርካታ ወገኖች ዘንድ መደናገር ተፈጥሮ ነበር” ብሏል።

አሁንም የተወሰነ ግርታ ውስጥ ያለው የኢህአዴግ አባል ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ የጠቀሰው አዲስ ራዕይ፤ “መንግሥትና ድርጅታችን ከመርህ የወጣ ነገር አልፈፀሙም” በማለት አባላቱን ተማጽኗል።

የግንባሩ መጽሔት አያይዞም፦” ከእስልምና ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን መደናገር በተመለከተ መጅሊሱ ምን እንደፈፀመና ለምንና እንዴት እንደሄደበት ለሕዝበ-ሙስሊሙ የማስረዳት ጉዳይ የመጅሊሱ ኃላፊነት ነው። መንግሥት ግን ቢያንስ የራሱን ድርሻ በወቅቱ በዝርዝር ማስረዳት አለመቻሉ ለእነዚህ ኃይሎች አፍራሽ ዘመቻ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል” ሲል ጽፏል።

አዲስ ራዕይ በዚሁ ዘገባው፤ “የአፍራሽ ኃይሎችን የሐሰት ዘመቻ በወቅቱ በተመጣጣኝ ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል ለሕዝቡ ትክክለኛውን ተግባር የሚያሳይ የኮሙኒኬሽን አግባብ ተነድፎ በተቀናጀ ሁኔታ አለመፈፀሙ፣ በዚህም ምክንያት አባላችንና ሕዝቡም ለሐሰት ፕሮፓጋንዳው በሰፊው እንዲጋለጡ መፈቀዱ፤ እንደክፍተት መውሰድ የሚገባው ነው” ሲልም ለችግሩ  አቶ በረከት የሚመሩትን የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ተጠያቂ አድርጓል።

አይጋ ፎረም በቅርቡ አቶ ስብሀት ነጋ-ከቪኢኤ ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ባተመበት ግርጌ፦”ዓለም በ አቶ መለስ ጤንነት ዙሪያ የተፈጠረበትን ብዥታ ለማጥራት የመንግስት ቃል አቀባይን እየጠበቀ ባለበት ሁኔታ ፤አንጋፋውና ልምድ ያካበቱት የህወሀት መስራች አቦይ ስብሀት ነገሩን ግልፅ አድርገውታል”በማለት እነ አቶ በረከትን በመንቀራፈፍ የሚወቅስ፤አቦይ ስብሀትን ደግሞ የሚያወድስ ጽሁፍ ማስፈሩ ይታወሳል።

“በሰላምና በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር፤ የዜጎችና የመንግሥት መብትም፣ ግዴታም ነው!” በሚል ርዕስ በአዲስ ራዕይ ላይ የሰፈረው ይኸው ዘገባ “አፍራሽ” ከተባሉት ኃይሎች ዘመቻ በተጨማሪ፤ ኢህአዴግ የውስጥ ድክመት እንደነበረም ያትታል።

“የአፍራሽ ኃይሎች ዘመቻ አንድ ነገር ሆኖ፤ በራሳችን በኩል ወጥ የሆነ ግልፅነት በመላው አባላትና አመራር አካላት ዘንድ ፈጥረን አለመግባታችንም የራሱ አሉታዊ ሚና ነበረው”ም ብሏል

“ ከሙስሊሙ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ለጥፋት ኃይሎች ዘመቻ ሰለባ በሆኑት ብዙሃን ንፁሃን ዜጎች መካከል የሚታየው የሰልፍ መዛነፍ ትክክለኛ ስፍራውን መያዝ አለበት” ያለው አዲስ ራዕይ፤  “ይህ እንዲሆን በቅድሚያ አባሉና አመራሩ በጉዳዩ ላይ የተሟላ ግልፅነት መያዝ አለባቸው”በማለት  በሙስሊሞች ጉዳይ የ ኢህአዴግ አመራሮችና አባሎች አንድ አቋም ሊይዙ እንዳልቻሉ ጠቁሟል።

ጽሁፉ ለኢህአዴግ አመራሮችና አባላቶች ባስተላለፈው ምክር፦ በችግሩ ዙሪያ ግልፅነት እንዲኖር  ከማሣሰቡም በተጨማሪ በዘፈቀደ የሚራመድ አቋምና ፤የሚሰጥ አስተያየት እንዲወገድ ያዛል።

“ጽንፈኝነት የሚያስከትለው ችግር፤ ሙስሊሙንም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ አባላችንን እንዲሁም መላውን ሕዝባችንን የሚመለከት ችግር እንደመሆኑ፤ በጋራ ትግል የምንፈታው ነው” ያለው የግንባሩ መጽሔት፤ “በምንም ዓይነት ሁኔታ በጥቅል ፍረጃ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ እንደሚያስፈልግ ይመክራል።

“የእምነቱ ተከታዮችና ተቋማት በሚፈፅሙትና ሊፈፅሙት በሚገባው ነገር እና እኛም እንደመንግሥት ልንሰራው በምንችለው ጉዳዮች ዙሪያ በተግባርም በአገላለፅም መደበላለቅ እንዳይኖር!” ሲል  ኢህአዴግ አባላቱን በጥብቅ አስገንዝቧል።

“አዲስ ራዕይ” መጽሔት ላይ በሚወጡ ጽሁፎች ላይ በየትኛውም ደረጃ ያሉ የኢህአዴግ አመራርና አባላት ተወያይተው የጋራ አቋም የሚይዙበት እንደሆነ የሰንደቅ ዘገባ ያስረዳል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ላይ ስጋት ለመፍጠር የተደረጉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በአስተማመኝ መልኩ ከሽፈዋል ብለዋል።

ድርጊቱን ለመግታት በተደረገ እንቅስቃሴ  የአንድም ሰው ሀይወት ሳይጠፋና  በንብረት ላይ የከፋ  ጉዳት  ሳይደረስ ፖሊስ ሀላፊነት በተሞላው መልኩ  በቁጥጥር ስር አውሎአል ብለዋል  ኮሚሽነር ጀነራል ወርቅነህ  ገበየሁ የተናገሩት።

ህገወጥ ድርጊቱን  ወደ  ክልሎች  ለማዛመትም  የተደረገው  ሙከራ መክሸፉንም ፖሊስ ገልጧል።

ፖሊስ ካወጣው መግለጫ በተቃራኒ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በመሪዎቻቸው እና በአማኒያን ላይ የተወሰደውን እርምጃ ለመቃወም በመጭው አርብ በብዛት እንዲገኙ መልክቶች እየተላለፉ ነው። ፖሊስ እንቅስቃሴውን አክሽፌዋለሁ ቢልም፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን  ግን መንግስት ሆን ብሎ ባቀነባበረው ወጥመድ ውጥስ ሳይገቡ መቅረታቸውን ነው የሚናገሩት። መንግስት በአንዳንድ አካባቢዎች የራሱን ካድሬዎች በመላክ ግጭት እንዲነሳ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide