ኀዳር ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ የሽግግር ካውንስል ለኢሳት በላከው መግለጫ የአፓርታይድ ስርአትን እአካሄደ ያለው የወያኔ አገዛዝ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ሊወገዝ ይገባዋል ብሎአል።
የኢኮኖሚ እድገት አምጥቻለሁ እያለ ፕሮፓጋንዳ የሚነዛ መንግስት ፣ በስልጣን ላይ ለመቆየት ብቸኛ መተማመኛው ሃይል መሆኑን አሳይቷል ያለው የሽግግር ካውንስል፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችና የአለማቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል።
ግንቦት7 በበኩሉ ድርጊቱን ፋሺስታዊ እርምጃ ሲል ገልጾታል። “ህወሓት ከስልጣን እስካልተወገደ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ፋሺስታዊ ተግባር መፈፀሙን የማይተው እኩይ ሃይል” ነው የሚለው ግንቦት7፣ የትግላችን ግብ ህወሃትን ማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግስት መመስረት መሆን አለበት ብሎአል።
ግንቦት 7፣ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. “መብቶቻችንን በህወሓት ዘረኛ አምባገነኖች አናስነጥቅም” በማለት አደባባይ የወጡ ወጣቶችን ጽናት ማድነቁን፣ ህወሓት የሚለውን ሳይሆን የይስሙላ ህጉ የፈቀደላቸውን ለማድረግ በመድፈራቸው በህወሓት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚደረገውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት
ማራመዳቸውንም አክሎ ገልጿል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህወሓት መወገዱ የማይቀር በመሆኑ ሠራዊቱ ራሱን ነፃ አውጥቶ ከሕዝብ ጋር እንዲወግንም ግንቦት7 ጥሪ አስተላልፏል።