በእስራት ላይ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በድጋሜ ተቀጠሩ  

ጥር ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲ  አመራሮች ለአራተኛ ጊዜ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡

የሰማያዊ፣  የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች ዛሬ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ለአራተኛ ጊዜ   የቀረቡ ቢሆንም፤  ፖሊስ ፦‹‹ምስክሮችን ማደራጀት ይቀረኛል›› በማለት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ለአራተኛ ጊዜ    የ28 ቀናት  ቀጠሮ መስጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ ሦስት ወር በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉት የፓርቲዎቹ አመራሮች፣ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም   ከታሰሩበት እለት አንስቶ እስካሁን ድረስ በወዳጆቻቸው  እንዳይጠየቁ   መከልከላቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ፖሊስ የሰነድ ምርመራውን በማጠናቀቁ ምንም ሊሰራው የሚችለው ተጨማሪ ስራ አልቀረውም›› ያሉት የታሳሪዎቹ ጠበቃ አቶ ገበየሁ፤ የፓርቲ አመራሮቹ ለተጨማሪ 28 ቀናት ማዕከላዊ እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ መፍቀዱ ተገቢ እንዳልሆነ የህግ አንቀጾችን በመጥቀስ  አስረድተዋል፡፡ ይሁንና የታሳሪዎቹን አቤቱታም ሆነ የጠበቃቸውን ማመልከቻ ያልተቀበለው ፍርድ ቤት፤ በፖሊስ በተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል።