ኢሳት (መጋቢት 18 ፥ 2009)
በእስራዔል ተላቪቭ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በመግባት ባንዲራ ያወረደውና ምልክቱን ያቃጠለው ኢትዮጵያዊ በፍድ ቤት በነጻ ተለቀቀ። ድርጊቱ ሲፈጸም በኢትዮጵያ የነበሩት አምባሳደር ጸጋዬ በርሄ የደህንነት ስጋት አለብኝ በማለት ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም። ሆኖም ተከሳሽ ኢትዮጵያዊ ከኤምባሲው 500 ሜትር እንዲርቅ ውሳኔ ተላልፎበታል።
ሃሙስ መጋቢት 14, 2009 በእስራዔል ቴላቪቭ ወደ ሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመግባት ባንዲራውን በማወረድ የኮከብ ሃውልቱን ገንጥሎ ያቃጠለው ወጣት ማስተዋል ጥላሁን ድርጊቱን የፈጸመው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ረገጣ በመቆጨት መሆኑን ገልጿል። ወጣት ማስተዋል ጥላሁን ለኢሳት እንደተናገረው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረው አቶ ሃብታሙ አያሌው በእስር ቤት የሚፈጸመውን ሰቆቃ ለቪኦኤ ሲናገር በሰማበት ወቅት በእልህ ድርጊቱን ፈጽሟል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ስርዓትና የስርዓቱን ድርጊት በመቃወም በተለያዩ የግዛት ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ላይ ተመሳሳይ ድርጊቱ ሲፈጸሙ መቆየታቸው ይታወሳል
በተለይ ዋሽንግተን የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያን በተቆጣጠሩበት ወቅት ኢትዮጵያውያኑ አክቲቪስቶች ላይ ጥይት የተኮሰው የኢምባሲው የጥበቃ ሰራተኛ በ48 ሰዓት ከአሜሪካ መባረሩ አይዘነጋም።
ቴላቪቭ ወደ ሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ በመግባት ባንዲራውን በማወረድ ኮከቡን ያቃጠለው ወጣት ማስተዋል ጥላሁን በድርጊቱ ፍርድ ቤት የቀረበ ቢሆንም፣ ፍ/ቤቱ በነጻ አሰናብቶታል። ሆኖም በኢትዮጵያ መንግስት በቀረበ አቤቱታ ከእንግዲህ ከኤምባሲው በ500 ሜትር ርቆ እንዲንቀሳቀስ ተወስኖበታል።