በእስራኤል እና በፍልስጤሞች መካከል ያለው ውጥረት እንደጨመረ ነው

ሰኔ ፳፭(ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድ ታፍኖ የተወሰደ የፍልስጤም  ወጣት መገደሉን ተከትሎ ፍልስጤማውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።

የ17 አመቱ ወጣት ሙሃመድ አቡ ካድር በመኪና ታፍኖ ሲወሰድ የአይን ምስክሮች ማየታቸውን ተናግረዋል።  ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ፖሊሶች ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ የእስራኤሉ መሪ ቤንጃሚን ናታንያሁ  ግድያውን አውግዘው፣ የእየሩሳሌም ከንቲባ የህዝቡን ቁጣ እንዲያበርዱ አሳስበዋል።

የፍልስጤም መሪዎች በበኩላቸው እስራኤል 3 ወጣቶች መገደላቸውን ተከትሎ የወሰደችው የበቀል እርምጃ ነው በማለት እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል።

ሃማስ ባወጣው መግለጫ እስራኤል ለዚህ ድርጊቷ አስፈላጊውን ዋጋ ትከፍላለች ብሎአል።

ሚ/ር ናታንያሁ እስራኤል በህግ የምትገዛ አገር መሆኗን ገልጸው ፖሊስ አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ የዚህን አሰቃቂ ግድያ ፈጻሚዎች ፈልጎ እንዲይዝ አሳስበዋል። ሁሉም ወገኖች ህጉን የራሳቸው መጠቀሚያ እንዳያደርጉት ጠ/ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የእየሩሳሌም ከንቲባ ግድያውን አውግዘው ሁሉም ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።

ልጆቻቸው የተገደሉባቸው የሶስቱ ወጣቶች ቤተሰቦችም  “ድርጊቱ የተፈጸመው ከልጆቻችን ግድያ ጋር በተያያዘ ከሆነ በጽኑ እናወግዘዋለን፤ የእስራኤልም ሆነ የአረብም ደም አንድ ነው፣ ወንጀል ወንጀል ነው” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል።

የፍልስጤሙ መሪ ሙሃመድ አባስ በበኩላቸው እስራኤል ከፍልስጤም ጋር ሰላም የምትፈልግ ከሆነ ድርጊቱን የፈጸሙትን በአስቸኳይ ለፍርድ ማቅረብ ይጠበቅባታል ብለዋል።