ጥር 8 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የእስራኤል ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ከስራ ሃላፊነቷ እንድትነሳ ያደረጋት የኢትዮጵያዊቷ ፀጋ መላኩ ጉዳይ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ መሆኑን የቴል-አቪቭ የጋዜጠኞች ማህበር ዳይሬክተር ዮሲ ባርሞሃ መናገራቸዉን ጀሩሳሌም ፖስት የተባለዉ ጋዜጣ ገልጿል።
ፀጋ መላኩ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት/እስራኤላዊ በመሆን የእስራኤል ረሸት አሌፍ የራዲዮ ጣቢያ ዳይሬክተር በመሆን ለሶስት አመታት በኮንትራት ስታገለግል የቆየች ሲሆን በሙያና ተግባሯ እጅግ ተቀባይነትን አግኝታ እንደነበር ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ካለፈዉ መስከረም ወር ጀምሮ አዲስ የተቋቋመዉ የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን አስተዳደር የኮንትራት ዉሏን ለማደስ ፈቃደኛ አልሆነም። በዚህም ምክንያት በስራዋ ምስጉን የሆነችዉ ሰራተኛ አላግባብ ከስራ በመሰናበትዋ በብሄራዊ የሰራተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርታ ጉዳዩ በመታየት ላይ ነው።
የቀድሞዉ የአይሁድ የዉጭ ሚዲያ አጄንሲ ቃል አቀባይ “ስደተኞች በቀላሉ የማያገኙትን ስራ ኢትዮጵያዊቷ ያገኘችዉ በችሎታዋ ተወዳድራ ባገኘችዉ ብልጫ ነዉ። አሁን ብሮድካስቲንግ ባለስልጣኑ እሷን ከስራ መደቡ ዝቅ ለማድረግ የወሰደዉ እርምጃ አሳፋሪ ነዉ፡ህዝብም መልዕክቱን መስማት ይኖርበታል።” በማለት የተወሰደዉ እርምጃ ተቀባይነት እንደሌለዉ ገልጿል።
በ16 ዓመት ዕድሜዋ በቤተ እስራኤላዊነቷ ወደ እስራኤል የተጓዘችዉ ፀጋ መላኩ ቀደም ሲል በሬዲዮ ጣቢያዉ የአማርኛ አገልግሎት ዉስጥ ስታገለገል የነበረችና በብሮድካስቲንግ ባለስልጣኑ ዉስጥ በጠቅላላዉ ለ23 አመታት ያገለገለች፤ በሁለት የትምህርት መስኮች በዩኒቨርስቲ የዲግሪ ትምህርቶችን የተከታተለች መሆኑ ታዉቋል።
በእስራኤል በኢትዮጵያዊያንና በሌሎችም ቤተ እስራኤላዉያን ላይ ዘረኝነትን ተመርኩዞ የሚደርሰዉ በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ እንዳለ ይነገራል።
በእየሩሳሌም ኪሪያት ማላኪ በተባለዉ አካባቢ ነዋሪዎች ቤታቸዉን ለኢትዮጵያዊያን ቤተ እስራኤላዊያን ላለማከራየትና ላለመሸጥ ያደረጉት ስምምነትና በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላቀረቡት አቤቱታና ተቃዉሞ የእስራኤል የስደተኛ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ ሶፋ ላንድቨር በሰጡት መልስ የተቀሰቀሰዉ ቁጣ እስካሁን አልባት እንዳላገኘ ይታወቃል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ታላቅ ህዝባዊ የተቃዉሞ ሰልፍ በነገዉ እለት የሚካሄድ ሲሆን በዚሁ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ሙሌት አራሮ የተባለ ኢትዮጵያዊ ቤተ እስራኤላዊ 63 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለዉን የሶስት ቀን ጉዞ ከመኖሪያዉ ኪሪያት ወደ እየሩሳሌም በትናንትናዉ ዕለት ጀምሯል።