ጥቅምት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በባሌ ዞን በጎባ ከተማ ቀበሌ 03 ልዩ ስሙ አዲስ ከተማ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ኤም ኦ ሲ ሚሺኒሪ ኦፍ ቻርቲ የተባለው ድርጅት በ1984 ሲቋቋም ዋና አላማው በዞኑ እና በአካባቢው የሚኖሩ እና እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ የአካል ጉዳት ያለባቸው ማለትም፤ መስማት እና ማየት የማይቸሉ፤ መራመድ የማይችሉ፤የአዕምሮ ዘገምተኞች፤እንዲሁም በዕድሜ የገፉ እና ጧሪ አልባ አዛውንቶችን ተቀብሎ ሲያስተናግድ እና ሲንከባከብ እንዲሁም ወላጅ አልባ ህፃናትን ተቀብሎ ማሳደግ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።
ይህ መንስታዊ ያልሆነ ድርጅት እነዚህን አገልግሎቶች ለመስጠት ዋና ገቢው ከውጭ በሚያገኘው ድጋፍ መሆኑን የውስጥ ሠራተኛ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ይጠቁማሉ፡፡
ድርጅቱ በቅርቡ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ በስሩ ታቅፈው የነበሩ አካል ጉዳተኞች፣ ማለትም የአዕምሮ ዘገምተኞች እና ታማሚዎች፣ ማየት እና መስማት የተሳናቸውን ታዳጊዎች እና አረጋውያንን ከመጠለያ ስፍራው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማባረሩ ፣ ጎስቋሎቹ፣ በከተማው ውስጥ እየተንከራተቱ እንደሚውሉና ለጎዳና ተዳዳሪነት እንደተዳረጉ ዘጋቢያችን ገልጿል። ከተባረሩት ዜጎች መካከል ቁጥራቸው በውል ያልተዋቀ ሰዎች ሞተዋል፡፡ እራሳቸውን ያጠፉ አዛውንት መኖራቸውም ይነገራል ፡፡
በብዛት ከአማራ ክልል እና አካባቢው የመጡት እነዚህ ዜጎች በአሁን ሠዓት ወዴት መሄድ እንዳለባቸው ባለማወቅ የጎባ ከተማ ጎዳና መኖርያቸው አድርገው ይኖራሉ፡፡
ይህ ድርጅት በአሁን ወቅትም ያልተዘጋ እና በሀገሩቱ ውስጥ ተመዝግቦ ያለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን ፣እኒህ ተጎጂዎች እስከ ፌደራል መስርያ ቤት ቢያመለክቱም ሰሚ በማጣት የሚመለከተው አካልም የጥቅም ትስስር እንዳለው በሚያሳይ መልኩ ተጎጂ እና ቅሬታ አቅራቢዎችን እስከ ማሰር እንደደረሰ ለማወቅ መቻሉን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያን እንደሚናገሩት እስካሁን በተወገዱት ተጎጂዎች ስም የሚመጣው እርዳታ እንዳልቆመ እና ይኸው እርዳታም ወዴት እንደሚገባ እንደማታወቅ ቁጥጥርም እንደማይደረግበት ድርጅቱም በማናለብኝነት እንዳሻው በወገኖች ላይ ግፉን እየቀጠለበ እንዳለ ታውቋል። እነዚህ የውጭ ሃገር ሰዎች ያሻውን የማሰሰር፣ የማባር እና አካል ጉዳተኞችን እስከ መብደብ የሚደርስ ግፍ እንደሚሰሩ እና የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናትም ሽፋን እንደሚሰጧቸው ዘጋቢያችን ያነጋጋራቸው ሰዎች ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የድርጅቱን ሃላፊዎች እና መንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።