(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 3/2009) በእሬቻ በአል በግፍ ለተገደሉት ሰዎች በአገዛዙ የቆመው የሰማእታት ሀውልት እንዲነሳ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/ጠየቀ።
ኦፌኮ የእሬቻ በአል መቃረብን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የሰማእታት ሀውልት ችግሩን ባደረሱትና ተጠያቂ ሊሆኑ በሚገባቸው አካላት መገንባቱ ከመሰረቱ ትክክል አይደለም።
ከመንግስት የሚጠበቀው የሟቾችን ማንነት በገለልተኛ አካል ይፋ ማድረግና የደም ካሳ ወይም ጉማ መክፈል እንዲሁም ገዳዮቹን ለፍርድ ማቅረብ ነው ብሏል።ኦፌኮ በመግለጫው
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/ መግለጫ እንዳመለከተው በእሬቻ በአል የዛሬ አመት አካባቢ መስከረም 22/2009 በግፍ የተገደሉ ዜጎችን ለማስታወስ በሚል የሰማእታት ሀውልት ተገቢ ባልሆነ ቦታና ተገቢ ባለሆነ አካል መሰራቱ አግባብ አይደለም።
ይህን ያለበትን ምክንያትም በመግለጫው ሲያብራራ በግፍ የተገደሉ ዜጎች ተለይተው ለመላው ሕዝብ ይፋ ባልተደረገበትና በገለልተኛ አካል ሳይጣራ ሐውልት ወይም ፓርክ ተሰርቷል መባሉን የሟች ቤተሰብም ሆነ ህዝቡ አይቀበለውም በሚል ነው።
የሰማእታት ሀውልቱ ችግሩን ባደረሱትና ተጠያቂ ሊሆኑ በሚችሉ አካላት መገንባቱም ትክክል አለመሆኑን ኦፌኮ በመግለጫው አመልክቷል።
እናም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ አገዛዝ የሟቾች ማንነት በግልጽ እንዲያሳውቁና ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ለተጎጅ ቤተሰቦች የደም ካሳ ወይም ጉማ መክፈልና ገዳዮችን ለፍርድ ማቅረብም እንደሚገባ ኦፌኮ በመግለጫው አመልክቷል።
ኦፌኮ ሀውልቱ ተገነባ ከተባለም በኋላ በቆመው ድንጋይ ላይ የሟቾቹ ስምና ምስል ሳይገለጽ ከጉዳዩ ጋር የማይመስል ሀተታ መቅረቡ አሳዛኝ ነው ብሏል።
በሀውልቱ ላይ በግፍ የተገደሉትን ዜጎች በድንገተኛ ሁኔታ የሞቱ መባላቸው ፌዝ መሆኑንም ኦፌኮ ጠቅሷል።
እናም ሀውልቱ ተጨማሪ ግጭት ከማስከተሉ በፊት ከቦታው እንዲነሳ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በመግለጫው ጠይቋል።