(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 5/2011) በኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ መነሳቱ ተገለጸ።
ለዘጠኝ ዓመታት የተጣለው ማዕቀብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ በሙሉ ድምጽ በመወሰን አንስቶታል።
ኤርትራ ውሳኔውን የዘገየ፡ ማዕቀቡም ህገወጥ ስትል ገልጻለች።
የኢትዮጵያ መንግስትም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ በመነሳቱ ደስታውን ገልጿል።
የማዕቀብ መነሳት የውሳኔ ሀሳብ የረቀቀው በእንግሊዝ መንግስት ሲሆን ባለፈው መስከረም ወር በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ጅቡቲና ሶማሊያ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ በይፋ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
በ2009 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነበር የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለው።
የሶማሊያውን አልሸባብ የተሰኘውን ድርጅት ታግዛለች በሚል የመሳሪያ ማዕቀብን ጨምሮ ባለስልጣናቷ ላይ የጉዞ ገደብና የሃብት እግድ ውሳኔ የተላለፈባት ኤርትራ ከመነሻው ክሱንም ሆነ ማዕቀቡን ህገወጥ ስትል ስታጣጥል ቆይታለች።
በወቅቱ የኢትዮጵያው አገዛዝ የሆነው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ህወሀት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በይፋ ከመጠየቅ ባለፈ በየጊዜው ማዕቀቡ እንዲራዘም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት የመርማሪዎች ቡድን ለአራት ተከታታይ ጊዜያት ጉዳዩን አጣርቶ ኤርትራ ለአሸባብ ድጋፍ ታደርጋለች የሚለው ክስ መሰረተ ቢስ ነው።
ያንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘሁም የሚል ሪፖርት ቢያቀርብም የጸጥታው ምክር ቤት ሪፖርቱን ወደጎን አድርጎን ማዕቀቡ እንዲራዘም ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ኤርትራ ማዕቀቡ እንዲራዘም በማድረግ የአሜሪካን እንጅ እንዳለበት በተደጋጋሚ ስትወቅስ ቆይታለች።
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ማዕቀቡ እንዲነሳ ምክንያት የሆነው በአፍሪካው ቀንድ እየታየ ያለው የሰላም አዝማሚያ ሊሆን እንደሚችል ቢነገርም በተለይ በኢትዮጵያው አዲስ አስተዳደር በኩል ማዕቀቡ እንዲነሳ የታየው ፍላጎት አስተዋጽዖ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላምና እርቅ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ተከትሎ በአፍሪካው ቀንድ የተጀመረው እንቅስቃሴ ለማዕቀቡ መነሳት ትልቅ ሚና እንዳለው ይነገራል።
ዶክተር አብይ አህመድም ማዕቀቡ እንዲነሳ በይፋ እንደሚጠይቁ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሶማሊያ ባለፈው መስከረም ወር በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት የጋራ ጥሪ የጸጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳው መጠየቃቸውም ይታወሳል።
ዛሬ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ተቀምጦ የዘጠኝ አመቱን ማዕቀብ እንዲነሳ አድርጓል።
በእንግሊዝ መንግስት የተረቀቀውን የወሳኔ ሀሳብ የጸጥታው ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ አጽድቆታል።
ለማዕቀቡ መጣልም ሆነ መራዘም ሚናዋ የጎላ የነበርችው አሜሪካ ዘግይታም ቢሆን በእንግሊዝ መንግስት በኩል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብላዋለች።
ውሳኔውን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት ምላሽ ሰጥቷል። ውሳኔውን በደስታ ተቀብዬዋለሁ ያለችው ኤርትራ ሆኖም የዘገየና ማዕቀቡም ሀገወጥ ነበረ ስትል ገልጻለች።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ማዕቀቡ በኤርትራ ላይ ከባድ ጉዳት ማምጣቱን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መነሳቱን አስመልክቶ የደስታ መግለጫ አስተላልፏል።
ውሳኔው በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በኢኮኖሚ፡ ማህበራዊናባህላዊ ትስስሮች ላይ አወንታዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው ብሎታል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀቡን ቢያነሳም በሶማሊያ ላይ የተጣለው የመሳሪያ ማዕቀብ ግን እንደሚቀጥል ታውቋል።