ግንቦት ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የብሔራዊ ፈተናን ምክንያት በማድረግ በመላው ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል። በኢንተርኔት መቋረጥ ገቢያቸውን በማጣት ባንኮች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የመረጃ ተቋማት ጨምሮ የሆቴል አገልግሎት ዘርፎች በቀዳሚነት ተጠቂ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳሉ።
በኢንተርነእት መቋረጥ ሳቢያ የገቢና ወጪ ንግድ የገንዘብ ልውውጥ ላይ ከፍተኛ እክል ተፈጥሯል። ድርጅቶቹ ላጋጠማቸው ኪሳራዎች በኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ በመንግስት በኩል ምንም ዓይነት ካሳ እንዳልተሰጣቸው ነጋዴዎቹ በምሬት ይናገራሉ። ሕዝባዊ እቢተኝነት በሚያጋጥምበት ጊዜያት እንዲሁም የብሔራዊ ፈተናን ተከትሎ ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ ዝግ ማድረግ በየትም አገራት ያልተለመደ አሰራር መሆኑን ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የውጪ አገር ቱሪስቶች የሚያደርጓቸው ጉዞዎች በአብዛሃኛው በመቀዛቀዙ በሆቴልዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከ380 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣታቸውን ባለፈው ሳምንት መገለጹ ይታወሳል። ሰሞኑን የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ የነበሩ ቱሪስቶች ጉዞዋቸውን መሰረዛቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።