በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመቆየት ወይም ለቆ ለመውጣት በሚሉ አማራጮ ላይ እየመከሩ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአውሮፓ ኩባንያዎች በሃገሪቱ ለመቆየት ወይም ለቆ ለመውጣት የሚሉ አማራጮ ላይ እየመከሩ መሆኑ ተገለጠ።

ኩባንያዎቹ በተለያዩ የክልል  ከተሞች ያለው ፖለቲካዊ ውጥረትና በቅርቡ በአንዳንድ ኩባንያዎች ላይ የተቃጣው ጥቃት በኢንቨስትመንት ስራዎቻቸው አማራጮችን እንዲመለከቱ እንዳስገደዳቸው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ረቡዕ ዘግቧል።

መቀመመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው የአፍሪካ ጁስ ሃላፊ የሆኑት አያን ዴሪ ባለፈው ወር በፋብሪካቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በአግባቡ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለጋዜጣው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በተካሄዱ የመሬት ቅርምት ላይ ጥናትን ሲያካሄድ የቆየው የኦክላንድ ኢንስቲትዩት በበኩሉ በመንግስት ተግባራዊ ሲደረገ የነበረው ይኸው ፕሮግራም በአርሶ አደሮች ዘንድ ቅሬታን እንዳስነሳ ለዘጋርዲያን ጋዜጣ ገልጿል።

ላለፉት አራትና አምስት አመታት በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ የነበሩ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሞች የአርሶ አደሮችን በምግብ እራስን የመቻል ተስፋ አደጋ ውስጥ እንደከተተው በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ላይ ጥናትን ያካሄደው ተቋም ምላሽን ሰጥቷል።

በአርሶ አደሮቹ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በመንግስ በኩል ምላሽ ባለማግኘታቸው ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሊቀሰቀሱና ስጋትን ሊፈጥሩ መቻላቸውንም ኦክላንድ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞ ጥቃት ደርሶባቸው የነበሩ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ተቋማት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

በቅርቡ ጥቃት የተፈጸመበት የአፍሪካ ዱሽ ኩባንያ ከመንግስት ጋር በሽርክና የሚሰራ ሲሆን፣ 10 በመቶ የሚሆነው የድርጅቱ ድርሻ የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ከዘጋርዲያን ጋዜጣ መረዳት ተችሏል።

ሬንሰን የተሰኘ ሌላ የአትክልት አምራች ኩባንያ ለመንግስት ቅርበት ባለው አንድ ግለሰብ የሚተዳደር እንደነበርና የጥቃቱ ሰለባ መሆኑን ጋዜጣው በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አስነብቧል።

ይሁንና የጥቃቱ ሰለባ የነበሩት የውጭ ኩባንያዎች ነዋሪው በመሬት መብት ዙሪያ ያለውን ቅሬታ በአግባቡ እንደሚያውቁ እና ከመንግስት ጋር በሽርክና መስራታቸው ለጥቃቱ ሊዳርጋቸው እንደሚችል መገንዘብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ምላሽን እንዲሰጥ ቢጠየቅም መልስ አለመስጠቱን የገለጸው የብሪታኒያው ጋዜጣ የኔዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ከመንግስት በኩል የጥበቃ ደህነት እንደተሰጠው አስታውቋል።

የኢንቨስትመንት ባለሙያዎች በበኩላቸው  አለመረጋጋቱ ገና ዕልባት ያላገኘ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው የጸጥታ ሃይሎች የሚያደርጉት ጥበቃ ዘላቂ ዋስትናን እንደማይሰጥ አስረድተዋል።

የኦክላንድ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አኑራዳህ ሚታል በበኩላቸው የውጭ ኩባንያዎች ሃገሪቱን በትክክለኛ መንገድ ለመደገፍ ፍላጎት ካላቸው ዜጎችን የሚጨቁን መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ስለማይችል ከሃገሪቱ ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።