በኢትዮ ሶማሊ ለሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ህዝቡ ድጋፉን እንዲሰጥ ተጠየቀ

በኢትዮ ሶማሊ ለሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ህዝቡ ድጋፉን እንዲሰጥ ተጠየቀ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ተወላጆች እንደገለጹት በክልሉ የሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ እየቀጠለ በመሆኑ ከክልሉ ተወላጆች ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ህዝባዊ እንቅስቃሴው ከተጀመረ በሁዋላ በርካታ የክልሉ ተወላጆች ተይዘው ታስረዋል። የአብዲ ኢሌን ጭካኔ የተሞላበት አገዛዝ ለመቃወም በውጭ አገር የተቋቋመው ዱል ሚዲድ አባላት ናቸው የተባሉ ወላጆች እና ቤተሰቦች እየተያዙ ነው። በተለይ የዱልሚድድ አባል የሆነው በስዊድን አገር ነዋሪ የሆነው አብዲፋታህ ጫባ በፌስ ቡክ ገጹ ህዝቡ ለመብቱ እንዲታገል መቀስቀሱን ተከትሎ እናቱ ወ/ሮ ሻሚስ ሃሳን ተይዘው ከታሰሩ በሁዋላ በእስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው አልፏል። አባቱ አቶ ሙሃሙድ አህመድ ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ ለከፍተኛ ህመም ቢደረጉም የአብዲ ኢሌ ደህንነቶች ልጃቸው ይቅርታ ካልጠየቀ በስተቀር አባቱ ህክምና እንደማያገኙ ተነግሯቸዋል። አባትየው ሽንታቸውን መቆጣጠር በማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸም ታውቋል።
የአብዲልፋታህ እህትም እንዲሁ ተይዛ ከታሰረች በሁዋላ፣ ደህንነቶች ለአብዱልፋታህ ስልክ በመደወል እንደሚደፍሯት ነግረውታል። በዚህ ሁሉ ስቃይ የተጨናነቀው አብዱልፋታህ ትናንት አብዲ ኤሌን ይቅርታ የሚጠይቅ ቪዲዮ በመስራት በፌስቡክ ላይ ለቋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸውው የቀድሞው የክልሉ የፖሊስ አባል የሆኑት ሻለቃ አሊ ሰምሬ በሌሎቹም የክልሉ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሽንሌና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሚካሄደው ተቃውሞ እየጠነከ በመሄዱ ኢትዮጵያውያን ከጎናቸው ሊቆሙ እና የአብዲ ኢሌ አገዛዝ እንዲያበቃ ሊታገሉ እንደሚገባ ሻለቃ አሊ ተናግረዋል። አብዲ አሌ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከ20 ሺ ያላነሱ የክልሉ ተወላጆች መገደላቸውን የገለጹት ሻለቃ አሊ ከ1 ሚሊዮን ያላነሱ ተወላጆች ደግሞ ተሰደዋል ብለዋል።