በኢትዮ-ሶማሊላንድ ድንበር በኮንትሮባንድ ነጋዴዎችና በልዩ ፖሊስ መካከል በተደረገ ግጭት 21 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2008)

ከሶማሊያ በተገነጠለችው ሶማሌላንድና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በኮንትሮባንድ ነጋዴዎችና በልዩ ፖሊስ መካከል በተደረገ ግጭት 21 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

ጋሻሞ ተብላ በምትጠራው በዚህ መንደር ለ21 ሰዎች ሞት መንስዔ የሆነው ግጭት፣ አሳዛኝ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት አብዲ ሞሃመድ ኦማር፣ ሃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ኮንትሮባንድ ጭኖ ይጓዝ የነበረን መኪና በሃይል ለማስቆም በመሞከራቸው የደረሰ አሳዛኝ ክስተት ማለታቸውን ጋራዌ ኦንላይን የተባለ ድረገጽ ዘግቧል።

አቶ አብዲ ሞሃመድ ኦማር በጋሻሞ መንደር የደረሰው የህይወት መጥፋት እሳቸው አውስትራሊያ በነበሩበት ወቅት የተከሰተ መሆኑን ገልጸው፣ የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን በአግባቡ ሳይዘግቡት የተሳሳተ መልክ ማስያዛቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ባለስልጣናትን ያቀፈ እውነት አፈላላጊ ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዲ ሞሃመድ፣ በልዩ ፖሊስና በአካባቢው ሚሊሺያ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ያጣራል ማለታቸውን ጋራዌ ኦንላንይ ዘግቧል።

በድንበሩ አካባቢ ሰፊ የንግድ ልወጥ የሚካሄድ ቢሆንም በተለያዩ ታጣቂዎችና በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች በንግድ ልውውጡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።

በሶማሊያ ከሚገኘው ታጣቂ ሃይል አልሻባብ ያፈነገጠና ራሱን ከአለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አይሲስ ጋር ግንኙነት እንዳለው ያወጀው አንድ ታጣቂ ሃይል በሶማሊላንድ መመሸጉ በድንበር ዙሪያ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ውጥረት የበዛበት እንዲሆን ማድረጉን የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል።

የበርበራን ወደም ለመጠቀም በድርድር ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በአመት እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የንግድ ልውውጥ እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።