ሰኔ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :- አቶ ግርማ ለፓርላማው ሁለት ሞሽን ያቀረቡ ሲሆን አንደኛው ሞሽን መንግስት በ2006 በጀት ዓመት የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ከመንግስት ባንኮች ሊበደር ያሰበውን 16 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በግማሽ ያህል (8 ቢሊየን ብር) በመቀነስ በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች የብድር ድጋፍ እንዲውል የሚጠይቅ ነው፡፡
ሁለተኛው የብሮድካስት ባለስልጣን ብሮድካስትን ከማስፋፋትና ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ለማቀጨጭ ተግቶ እንደሚሰራ፣ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳይኖር ያደረገ ደካማ መ/ቤት መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ በጀት ከሠራተኞች የደመወዝ በጀት በስተቀር እንዳይፈቀድለት፣ወደፊትም እንዲዘጋና ፍቃድ የመስጠት ስራ በሌሎች መ/ቤቶች ተደርቦ እንዲሰራ የሚጠይቅ ነበር፡፡
አቶ ኃ/ማርያም ይህንን ሞሽን በመቃወም በሰጡት ምላሽ ባለስልጣኑ ከ20 የማያንሱ የማህበረሰብ ራዲዮ፣ 5 የግል ራዲዮ ጣቢያዎችን ፣በየክልሉ የመንግስት ቴሌቪዝን ጣቢያዎች እንዲስፋፉ መስራቱን፣ ማስታወቂያ ሚ/ር ሲፈርስ የፕሬስ ቁጥጥር ወደእሱ መምጣቱን፣ የማስታወቂያ አዋጅ ስልጣን የሚሰጠው ለሱ መሆኑን በመዘርዘር በተዘዋዋሪ ሥራ የሚበዛበት ተቋም በመሆኑ መፍረስና በጀቱም መቀነስ እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም የብሮድካስን ስርጭትን ወደ ዲጂታል ለማዛወር እየተሰራ መሆኑን፣ ባለሃብቱንም ያን ጊዜ ማሳተፍ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ጠ/ሚኒስትሩ በአቶ ግርማ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ የብሮድካስት አዋጁ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለግል ባለሃብቶች ለመፍቀድ የሚያስችል ሆኖ እያለ በተግባር ለምን ተከለከለ በሚል ለሚነሱ ቅሬታዎች ምንም ዓይነት ማብራሪያ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡
የብሮድካስት አዋጅ ከወጣ ከ12 ዓመታት በላይ የተቆጠረ ቢሆንም ባልታወቀ ሁኔታ ባላስልጣኑ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ፈቃድ ለባለሃብቶች ለመስጠት አልቻለም፡፡ በአንድ ወቅት አቶ በረከት ስምኦን ስለጉዳዩ በፓርላማ አባላት ተጠይቀው የሕዝቡ ንቃተ ሕሊና ባልዳበረበት ሁኔታ የግል ቴሌቪዥን መፍቀድ እንደማይቻል በመጥቀስ አስፈጻሚው አካል ከሕግ አውጪው በላይ መሆኑን በተግባር ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተያዘም ፓርላማው ያልተጠበቁ ተሿሚዎችን ተቀብሎ አጽድቋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርን ከወ/ሮ ገነት ዘውዴ ቀጥሎ ገድለውታል በሚል ክፉኛ የሚተቹትን አቶ ደመቀ መኮንን ከተደራቢ የትምህርት ሚኒስትር ሃላፊነታቸው በማንሳት በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ሥራቸው እንዲቀጥሉ፤ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከክልል ፕሬዚዳንትነት በማንሳት የትምህርት ሚኒስትር አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ አማካሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን በአቶ በረከት ስምኦን ምትክ የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር፣ አቶ መኮንን ማንያዘዋልን ወደፕላን ኮምሽን በማዛወር በእሳቸው ምትክ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር በመሆን አቶ አህመድ አብተው፣ የአዲስአበባ ከንቲባ እንደሚሆኑ እየተነገረላቸው ባሉት አቶ ድሪባ ኩማ ምትክ የትራንስፖርት ሚኒስትር የፖሊስ ኮምሽነር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ ተሹመዋል፡፡
በተጨማሪም የኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ወደክልል በተዛወሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ ምትክ ወ/ሮ ሮማን ገ/ስላሴ በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር፣ በድክመት በቅርቡ በተነሱት አቶ ብርሃን ኃይሉ ምትክ አቶ ጌታቸው አምባዬ የፍትህ ሚኒስትር፣ በሙስና በተከሰሱት አቶ መላኩ ፈንታ ምትክ አቶ በከር ሻሌ በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ በአካባቢ ሳይንቲስቱ በዶ/ር ተወልደ ገ/እግዚአብሔር ምትክ አቶ በለጠ ታፈረ የአካባቢና ደን ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ለፓርላማ ሳያቀርቡ በትላናትናው ዕለት በሥራ አፈጻጸማቸው ደካማ የሆኑትን እና የሕዝብም ድጋፍ የራቃቸውን አቶ በረከት ስምኦንን እና አቶ ኩማ ደመቅሳን በሚኒስትር ማዕረግ የጠ/ሚኒስትሩ የጥናትና ምርምር አማካሪ አድርገው መሾማቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ የህዝብ ግንኙነት ሥራ ድክመት መኖሩንና ስራውን ለማጠናከር መታሰቡን የገለጹ ሲሆን የአቶ በረከት መነሳት ከዚሁ ትችት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ሪፖርተርና ፎርቹን ጋዜጦች አቶ በረከት በአለቃ ጸጋየ በርሄ የተያዘውን የጸጥታ አማካሪነቱን ቦታ ይይዛሉ በማለት መዘገባቸው ይታወቃል። አንዳንድ ወገኖች አዲሱ ሹመት የአቶ በረከት የስልጣን ፍጻሜ መጨረሻ መጀመሪያ ነው በማለት ከአቶ አርከበ እቁባይ ታሪክ ጋር በማዛመድ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይሰማሉ።
ጠ/ሚኒስትሩ በዛሬው ሹመት ይካተታሉ ተብለው የተጠበቁትን የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነር፣ የመረጃና ደህንነት ሚኒስትር ሹመቶችን ሳያቀርቡ ቀርተዋል፡፡