ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከዚህ ቀደም በ1997 ምርጫ ወቅት በቅንጅት መሪዎች፣ በጋዜጠኞችና በሲቪክ ተቋማት መሪዎች ላይ የቀረበው ክስ ፣ 24 ሰአታት አስቂኝ ፊልም የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። በፍርድ ቤቱ የነበረውን ሁኔታ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የቃሊቲው መንግስት በሚል ርእስ ዘርዝሮ ማቅረቡ ይታወቃል።
በቅርቡ አይ ኤስ ኤስ የተባለው አሸባሪ ድርጅት በ30 ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰደውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ለማውገዝ መንግስት በጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ተቃውሞ መርተዋል፣ በተቃውሞው ተሳትፈዋል እየተባሉ በእስር በሚሰቃዩ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ክስም እንዲሁ ፈገግ እያሰኘ ነገር ግን በዚያው ልክ እያሳዘነና አገራችን የገባችበትን የወርደት ደረጃ እያመላከተን ነው።
ቴዎድሮስ አስፋው ፣ ያሬድ ደመቀና አንዋር ከድር በተባሉ ወጣቶች ላይ የቀረበው ክስ እንዲህ ይላል ” ተከሳሽ የሃሰት ወሬዎችን በማውራት ጥላቻና የፖለቲካ ሁከት ለመቀስቀስ በማሰብ በ14/08/07 ዓም ከጧቱ 12 ሰአት ሲሆን በአዲስ አበባ ክ ከተማ በ01/02/03 በአሸባሪዎች ጥቃት ምክንያት ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሰዎችን በመሰብሰብ ” መለስ የሞተው ደንግጦ ነው፣ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቁሙ የሞተ ነው” የሚል ሃሰተኛ ወሬዎችን በማውራት ሁከት መቀስቀስ ወንጀል ተከሷል። ”