(ኢሳት ዜና–መስከረም 15/2010)በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በጎሳዎችና በብሔሮች መካከል ሆን ብሎ እየቆሰቆሰና እየፈጠረ ካለው ግጭት እንዲቆጠብ የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ባወጡት መግለጫ አሳሰቡ።
በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ አተኩሮ በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደውና በቪዥን ኢትዮጵያና ኢሳት ትብብር የተዘጋጀው ሀገራዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች አገዛዙ ሰዎችን ከመግደልና ከማንገላታት እንዲሁም የግለሰብ ነጻነትን ከመድፈር እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
ሕዝቡም አንድነቱን እንዲጠብቅ ጉባኤተኞቹ ጥሪ አቅርበዋል።
4ኛ የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ገምግሟል።
እናም የአገዛዙ አደገኛ ፖሊሲዎች በተለይም በከፋፍለህ ግዛው የሕወሃት ሴራ ምክንያት በምስራቅ ኢትዮጵያ የሶማሌ ጎሳ አባላትን ከኦሮሞዎች ጋር እንዲጋጩ በማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፥ ከ70 ሺ በላይ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።
የሕወሐት አገዛዝ ወንጀሉን ከፈጸሙት ጋር ከበስተጀርባ ተባባሪ በመሆኑ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ኮንፈረንሱ ከተጠናቀቀ በኋላ በወጣው መግለጫ ተመልክቷል።
ይህ ብቻ አይደለም ይላል መግለጫው የጉጂ ኦሮሞዎችንም ከኮሬና ቡርጂ ጎሳዎች ጋር አገዛዙ እያጋጫቸው ነው ተብሏል።የአፋርን ሕዝብ ከአማራው ጋር እንዲጋጭ እየተደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በአፋር፣ጋምቤላ፣ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ኦሮሚያና በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ካለምንም ካሳ ከመሬታቸውና ከቀያቸው በአገዛዙ አማካኝነት ተፈናቅለዋልም ተብሏል።
እናም እነዚህን ወቅታዊና አሳሳቢ ሁኔታዎች በመገምገም የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የአቋም መግለጫ አውጥተዋል። አገዛዙ ከዚህ አጥፊ ተግባር እንዲቆጠብ በማሳሰብ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ የአቋም መግለጫውን ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል።
በቪዥን ኢትዮጵያና በኢሳት ትብብር በተዘጋጀው ሀገራዊ ኮንፈረንስ ላይ ምሁራን የተለያዩ ጽሁፎችን በማቅረብ ውይይት እንዲካሄድባቸው አድርገዋል።
በውይይቱ በቅርቡ በአሜሪካ ኮንግረስ ድምጽ ይሰጥበታል የተባለው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበርና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር እንዲኖር ግፊት በሚያደርገው ኤች አር 128 ላይም ውይይት ተደርጓል።
እናም ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያው አገዛዝ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚኖረው በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካባቢያቸው ያሉ ኮንግረስማኖች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
በቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ላይ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር/ኦዴግ/፣የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሃይልና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ ተወካዮች በሀገራዊ የአንድነት መንፈስ ትግሉን አስተባብሮ ለአንድ ኢትዮጵያ መታገል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።ዶክተር መስፍን አብዲ ኦዴግን በመወከል ኢትዮጵያን በጋራ ተሰልፈን እናድናት ብለዋል።