በኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋት ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አንድ አለም አቀፍ ተቋም ገለጸ

ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2015)

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በሃገሪቱ ያለው አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ግሎባል ሪስክ ኢንሳይት (Global Risk Insight) የተሰኘ የፋይናንስ ተቋም ማክሰኞ አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ የሚገኘው ይኸው ተቃውሞ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ በውጭ ባለሃብቶች ዘንድ ስጋትን እንደሚፈጥር ተቋሙ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ያለው የኢኮኖሚ እድገት ሁሉን አሳታፊ መሆን እንዳለበት ያሳሰበው ድርጅቱ በልማት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በቂ ካሳ ማግኘት እንደሚገባቸውም የፋይናንስ ተቋሙ አመልክቷል።

በሃገሪቱ ያለው የኢኮኖሚ እድገት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገም በልማት ምክንያት የተፈናቀሉና ትኩረት ያላገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥያቄያቸው በአግባቡ ምላሽን ሊያገኝ እንደሚገባ ተቋሙ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሃገሪቱ ከአሜሪካና ከሌሎች ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያሻክር እንደሚችልም ግሎባል ሪስክ ኢንሳይት ተቋም አክሎ አስታውቋል።

አለም-አቀፍ ትክረትን ስቦ የሚገኘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ከአሜሪካ ከበርካታ አካላት ዘንድ ቅሬታን ማስከተሉ ይታወሳል። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ በትንሹ 150 ሰዎች መሞታቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩም ለእስር መዳረጋቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

የሟቾችንና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር ከመግለጽ የተቆጠበው መንግስት በበኩሉ የማስተር ፕላኑ እቅድ እንደማይካሄድ በመግለጽ ተቃውሞ ለማብረድ ጥረት እያደረገ ይገኛል።