የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ እየወሰደ ያለው የእስር እርምጃ አሳስቦኛል አለ

በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለው የእስር ዘመቻ ስጋት እንዳሳደረበት የአሜሪካ መንግስት በድጋሚ ገለጠ።

ተቃውሞውን ተከትሎም ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱና በሃገሪቱም ሃሳብን በነጻነት የመግለጥ መብቱ እንዲከበር አሜሪካ አሳስባለች።

የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል-አቀባይ የሆኑት ኔድ ፕራይስ ሃገራቸው ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞችንና ሌሎች ሰዎችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረቧን ሃላፊው ዋቢ በማድረግ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

መንግስት ተግባራዊ አድርጎ የሚገኘውን የጸረ-ሽብር አዋጅንም የሰብዓዊ መብቶችን ለማፈን ማዋል እንደሌለበት ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት ተመሳሳይ ስጋቷን የገለጸችው አሜሪካ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ሁኔታ አሳስቧት እንደሚገኝም በድጋሚ አስታውቃለች።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ሃገሪቱ በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ የሆነ አቋም እንድትከተልና እርምጃዎችን እንድትወስድ በማሳሰብ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ እየታየ ነው የሚባለው ልማት ኢኮኖሚያዊ እድገት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ፣ በሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና የሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ሚስተር ኔድ ፕራይስ አክለው አስታውቀዋል።

ለአንድ ወር ያህል ጊዜ በቀጠለው በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ፣ እስከአሁን ድረስ ከ100 በላይ የሚገመቱ ሰዎች እንደሞቱ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡና መንግስት ጥያቄን በሚያነሱ ሰዎች ላይ የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እንዲያቆም ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ተቃውሞውን ተከትሎ ከ4ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁለት ጋዜጠኞችም የዚሁ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል።