(ኢሳት ዜና–መስከረም 18/2010) በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር በኤምባሲው ሰራተኞች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈጸማቸው ከስራቸው መባረራቸው ታወቀ።
በአዲስ አበባ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አምባሳደር ኪም ሙንሁዋን የቀረበባቸውን የወሲባዊ ትንኮሳ ድርጊት ሲመረምር የቆየው የደቡብ ኮሪያ መንግስት የዲሲፒሊን ቦርድ በድርጊቱ ተጠያቂ ስላደረጋቸው ከሃላፊነት እንዲነሱ ተወስኗል።
ማክሰኞ ከአምባሳደርነታቸው የተባረሩት ሚስተር ኪም ሙንሁዋን በበርካታ የኤምባሲው ሴት ሰራተኞች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈጸም እንዲሁም ከኤምባሲው ጋር የስራ ግንኙነት ባላቸው ተቋማት ሰራተኞችም ላይ ይኽንኑ እኩይ ባህሪያቸውን በማንጸባረቃቸው መወገዳቸው ታውቋል።
አምባሳደሩ በአንዲት የኤምባሲው ባልደረባ ላይ የፈጸሙት አስገድዶ የመድፈር ድርጊትም ከስልጣን ለመባረራቸው ዋናው ምክንያት እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ጉዳያቸው በሕግ መያዙም ታውቋል።
አቃቢ ህግም ጉዳዩን በመመርመር ላይ መሆኑም ተመልክቷል።