በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዝሬ ዕጥረት መፈጠሩን፤ በዚህም ሳቢያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መቸገራቸውን፤ ሪፖርተር ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ዘገበ:: አሁን ለተከሰተው የውጭ ምንዛሬ እጥረት፤ በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ከሐገር በመውጣቱ እንደሆነ ሪፖርተር ባለሞያዎችን ጠቅሶ አመልክቷል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የኢኮኖሚክስ ባለሞያ፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻውም፤ ለምንዛሬ እጥረቱ ምክንያት፤ ገንዘብ በህገ-ወጥ መንገድ እየወጣ በመሆኑ ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በሐገሪቱ የተከሰተውን የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ተከትሎ፤ ዕቃ ወደ ሐገር ቤት የሚያስገቡ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሬ ባለማግኘታቸው ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት ባለመቻላቸው የንግድ እንቅስቃሴያቸው መስተጓጎሉ ታውቋል::
አሁን በሐገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሬ አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ማለትም ለመድሀኒት ለነዳጅ እና ለመሳሰሉት ብቻ እንደሚውልም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሳወቁ በዘገባው ተመልክቷል::
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት የተከሰተው የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊን መሰወር ተከትሎ በተፈጠረው አለመረጋጋት እንደሆነም ተገልጿል:: ሐገሪቱ በብድርና ዕርዳታ እንዲሁም በውጭ ንግድ ከተገኘው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ባሻገር በውጭ ሐገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚላከው የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ባደገበት ሁኔታ ዕጥረት መከሰቱ ያልተጠበቀ ሆኗል::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለስልጣናት በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በ9 ወራት ብቻ በውጪ ሐገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ማለትም በባንክ በኩል ወደ ሀገር ቤት የተላከው ገንዘብ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል::
የኢኮኖሚክስ ባለሞያው ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ለኢሳት እንደተናገሩት፤ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሐገር ቤት የተላከው ገንዘብ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ያህል መሆኑን በጥናት እንደደረሱበት አመልክተዎል።
በባንክ በኩል ሳያልፍ በሌላ መስመር ወደ ሐገር ቤት የሚገባ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መኖሩም በባለሞያዎቹ እየተገለጸ ይገኛል::
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሁኔታ በባለስልጣናት እና ለሥርዓቱ ቅርብ በሆኑ የንግድ ማህበረሰቡ አባላት ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋት ማስከተሉን ከአዲስ አበባ ያስረዳሉ::