ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2008)
መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች በአግባቡ አልተስፋፋባትም በምትባለው ኢትዮጵያ የካንሰር በሽታ በየአመቱ 44ሺ ሰዎችን እንደሚገድል የጤና ባለሙያዎች ሃሙስ ይፋ አደረጉ።
ይኸው በአደጉ ሃገሮች ብቻ ይታወቅ የነበረው የካንሰር በሽታ ከሚገድላቸው ሰዎች በተጨማሪ ወደ 70ሺ የሚጠጉ ሰዎች በዚሁ በሽታ እንደሚያዙም የቱርኩ አናዱሉ የዜና አውታር ዘግቧል።
የካንሰር በሽታ በኢትዮጵያ አሳሳቢ የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን የገለጹት የጤና ባለሙያዎች ይኸው በሽታ በሃገሪቱ በየአመቱ ከሚሞቱ አጠቃላይ ሰዎች መካከል ወደ 6 በመቶውን እንደሚሸፍን አስታወቀዋል።
እድሚያቸው ከ75 አመት በታች በሆኑ ሰዎች በካንሰር በሽታ የመያዙ እድል 11.3 በመቶ መድረሱንም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካንሰር መቆጣጠሪያና የበሽታዎች መከላከያ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ኩንዝ አብደላ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በሚገኘው የካንሰር በሽታ ሴቶች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ሲሆኑ በየአመቱ ከሚሞቱት 44ሺ ሰዎች መካከል ሁለት ሶስተኛ እጅ ሴቶች መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል።
የጡት፣ የማህጸንና፣ የአንጀት ካንሰር በሃገሪቱ በብዛት ኣየታዩ የመጡ በሽታዎች መሆናቸውን የገለጹት የጤና ባለሙያዎች ጉዳዩ አሳሳቢ የጤና እክል እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።
በሃገሪቱ የካንሰር በሽታ መስፋፋትን ተከትሎም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታውን ለመከላከልና ቀድሞ ለማወቅ እንዲሁም ለማከም የሚረዳ የአምስት አመት ብሄራዊ የካንሰር እቅድ መንደፉንም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የካንሰር ታማሚዎችን ለመርዳት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ጥረትን እያደረገ እንደሚገኝ የዜና ወኪሉ በዘገባው አስፍሯል።
በበለጸጉ ሃገራት ያለን የኑሮ ሁኔታና የአመጋገብ ስርዓት ተከትሎ ይከሰታል የሚባለው የካንሰር በሽታ አሁን አሁን በማደግ ላይ ባሉ ሃገራትም በመከሰት ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 2030 ድረስም ወደ 13 ሚሊዮን የሚደርስ ሰው በካንሰር በሽታ እንደሚሞትም ይነገራል።