በኢትዮጵያ የአደገኛ አደንዛዥ ዕፅ ምርት እየጨመረ ነው ተባለ

ጥቅምት ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የህወሀት ንብረት የሆነው ፋና ራዲዮ ”  ካናቢስ የተባለው የአደንዛዥ ዕፅ ምርት በአዲስ አበባ ፥ ለመልሶ ማልማት የታጠሩ አካባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ ክልል ፣ በኦሮሚያ ፣ አርሲና ምስራቅ ሃረርጌ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በአባይ በረሃ በስፋት እንደሚታይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መናገሩን” በመግለጽ ዘግቧል።

ባለፈው ዓመት ብቻ መጠኑ ከ400 ኪሎ ግራም በላይ እንዲሁም ያልተመዘነ 8 ቁምጣ የካናቢስ እፅ በኮሚሽኑ መያዙንም ኮሚሽኑ መግለጹን ራዲዮው ዘግቧል።

በሻሸመኔ በ1408 ስኩየር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተተከለ ካናቢስ መገኘቱን ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ ድርጊት ተሳትፎ ያላቸውን 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተገልጿል።

 

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ አደንዛዥ እጽ ብቻ ሳይሆን መጠናኛ አነቃቂ የሆኑ እጾችንም የሚወስዱ ሰዎች ተበራክተዋል።  በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች የጫት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ የምግብ ፣ መድሀኒትና የጤና እንክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች ለአደገኛ ዕፅና ሌሎችም ሱሶች መጋለጣቸውን በጥናት አረጋግጧል ።

ባለስልጣኑ በቅድመ ጥናት ኣካቶ ካያቸው ዩኒቨርስቲዎች መካከል የአዲስ አበባ ፣ ሀዋሳ ፣ ባህር ዳር ፣ ጎንደር ፣ ጅማና ሀሮማያ ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል ።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከስራ እጦት፣ ተስፋ ከመቁረጥና ከራእይ እጦት ጋር በተያያዘ ለአደጋኛ እጾች እየተጋለጡ መምጣታቸውን ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት።