በኢትዮጵያ የአእምሮ በሽተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው

ታኀሳስ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከቅርብ ኣመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤና መቃወስን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፉ መምጣታቸውን፣ መንግስትም ችግሩን ለመከላከል በቂ የሆነ ጥረት እንዳላደረገ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡
ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል የካንሰር ሕመም ፣ የአእምሮ ህመም፣ ከውፍረት ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች፣ ከአልኮልና የትምባሆ እንዲሁም ከአደገኛ ዕጾች ጋር የተያያዙ የጤና ቀውሶችና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ችግሮቹን ከመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ጋር አቀናጅቶ ለመስራት ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ችግሩ ካለበት ስፋት አንጻር ባለፉት ኣመታት የተገኘው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ሪፖርቱ ተላላፊ ያሆኑ በሽታዎች በቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን እየተበራከቱ መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ ካለ በኍላ፣በተለይ በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች የውፍረት መጠን መጨመር፣ አልኮልና የትምባሆ እንዲሁም አደንዛዥ እጾች ተጠቃሚነት መበራከት፣ የአእምሮ ጤና መቃወስ (ድብርት፣ ጭንቀት) እንዲሁም የአየር ብክለት፣ ኬሚካሎች ልቀት እየተበራከቱ መጥተዋል ይላል፡፡
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለማከም የሚወጣው ወጪም ሆነ የሚያስፈልገው አቅም ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እነዚህ በሽታዎች እንዳይስፋፋ የተደረገው ጥረት አመርቂ እንዳልነበር ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡