ሐምሌ ፲፰(አስራ ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2005 ጀምሮ ወደአሜሪካን ለሚጓዙ ሁሉ የቪዛ ሒደትን የሚያቃልል አዲስ አሰራር እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ኤምባሲው ትላንት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንደጠቀሰው የአሜሪካን ኤምባሲ የቪዛ ሒደት ክፍያን ከፍለው ቀጠሮ ያስያዙ አመልካቾች ከሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በፊት ቀጠሮ እንዲይዙ በጥብቅ አሳስቧል፡
ቀጠሮአቸውም ከሐምሌ 24 ቀን 2005 በፊት ማስያዝ ያልቻሉ አመልካቾች የቪዛ ማመልካቻ ክፍያውን ለመክፈልም ሆነ ቀጠሮ ለመያዝ አዲሱ አሰራር ተግባራዊ እስከሚሆንበት ሐምሌ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
የቪዛ ማመልከቻ ክፍያውን ከሐምሌ 24 ቀን 2005 በቀድሞ አሰራር መክፈልና ቀጠሮውን ደግሞ በአዲሱ አሰራር ከሐምሌ 24 ቀን 2005 በኃላ ማስያዝ የቪዛ ማመልከቻ ክፍያውን በድጋሚ መክፈል ሊጠይቅ እንደሚችል ኤምባሲው አስጠንቅቋል፡፡
አዲሱ አሰራር በቪዛ ማመልከቻ ክፍያ ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ እንደማያስከትል መግለጫው ጠቅሶ ይህ አዲስ አሰራር አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እያደረገ ያለው ጥረት አካል ነው ብሎአል፡፡ ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ካስፈለገ በኤምባሲው ድረገጽ ላይ ሰሞኑን ፈልጎ ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁሟል፡፡