በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መምጣቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መምጣቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
(ኢሳት ዜና የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) በመላው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ እና የዋጋ ግሽበቱ ባስከተሉት ጫናዎች ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት እየናረ እንደሚገኝ ተነገረ።
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዛሬ ባወጣው ወርሃዊ የዋጋ ንረት ልኬት ቀመር መሰረት በየካቲት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በ15 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጿል።
እንደ ድርጅቱ መግለጫ ምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች ካለፈው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በ9 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ደግሞ 9 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሬ ታይቶባቸዋል። የእህል፣ የጥራጥሬ፣ የአትከልትና የፍራፍሬ እንዲሁም የበርበሬና ቅመማ ቅመም ዋጋ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ሲሆን፣ እነዚህ ምርቶች በየካቲት ወር ብቻ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ከሃምሳ ከመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን ገልጿል።
የኑሮ ውድነቱ በመላው ኢትዮጵያ የተከሰተ ቢሆንም፣ በተለይ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ክልል የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች መፈናቀልን ተከትሎ የምርት ተአቅቦ በመደረጉ፣ የዋጋ ንረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በጂጂጋ አንድ ቲማቲም እስከ አምስት ብር እየተሸጠ መሆኑን ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል።