ሚያዝያ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከወር ወር እየባሰበት መምጣቱን የኢትዮጵያ ስታስቲክ ኤጀንሲ ወርሃዊ ጥናት አመላክቷል። ድርጅቱ ባወጣው ዝርዝር ጥናት መሰረት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የምግብ ሸቀጦች ከነበሩበት 9 ነጥብ 6 ከመቶ ወደ 12 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል። ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች በበኩላቸው በመጋቢት ወር ከነበሩበት 4 ነጥብ 6 ከመቶ ወደ 7 ነጥብ 3 ከፍ ማለቱን ኤጀንሲው አስታውቋል።
በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል የኢትዮጵያ የአደጋ መከላከልና ዝግጅት ኮሚሽን ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።