በኢትዮጵያ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳስቦኛል ስትል ኖርዌይ አስታወቀች

ኢሳት (ጥቅምት 22 ፥ 2009)

በኦሮሞና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳስቦኛል ስትል ኖርዌይ ስጋቷል ገለጸች። የአውሮፓ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ በፖለቲካ አለመረጋጋት ስትሰቃይ ማየት በጣም ያሳስባል በማለት የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ፈጣን የፖለቲካ ማሻሻያ ሳይውል ሳያድር መውሰድ ይኖርበታል ያሉት የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ቦርግ ብሬንዴ (Borge Brende) ፣ በአገሪቷ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታም መንግስታቸው በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከአጋራችን ኢትዮጵያን ጋር ሰላም በሚሰፍንበት ሁኔታ ላይ መነጋገራችንን መቀጠል እፈልጋለሁ ሲሉ ተናገረዋል።

ሚስተር Brende በአገሪቷ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋትና ያንን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እጅግ አሳስቦኛል ካሉ በኋላ፣ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አስረድተዋል። ከኢትዮጵያ ህዝብ ግማሹ ወይም 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች ስራ በመፈለግ የተሰማሩ፣ የመናገር ነጻነት እንዲከበርላቸው የሚፈልጉ እና በአገሪቷ የፖለቲካ ሂደት ተሳትፎ ማድረግ የሚፈልጉ መሆናቸውን ሚስተር ብሬንድ አስረድተዋል።

ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ የምስራቅ አፍሪካን የጎበኙት ሚስተር ብሬንድ የደቡብ ሱዳን፣ የኬንያ፣ የሶማሊያና ኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናንት ማነጋገራቸው ታውቋል። ኢትዮጵያን በጎበኙ ጊዜም አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዳነጋገሯቸው ታውቋል።