በኢትዮጵያ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአራት ወር እንዲራዘም ተደረገ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2009)

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ሊውል ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ተወሰነ።

የአዋጁን አፈጻጸም ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሃሙስ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ እና ጸረ-ሰላም ሲል የገለጻቸው አካላት እየተንቀሳቀሱ ነው ሲል አስታውቋል። በበራሪ ወረቀቶች የተለያዩ ፅሁፎች አሁንም ድረስ በመበተን ላይ እንደሚገኙ ኮማንድ ፖስቱ ለፓርላማ ገልጿል።

የኮማንድ ፖስት ጸሃፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ አለመያዛቸውንም ለፓርላማ አባላቱ በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።

ይሁንና አቶ ሲራጅ ጸረ-ሰላም ሃይሎች ሲሉ የገለጿቸው ሃይሎች በሃገሪቱ በየትኛው ስፍራ እንደሚንቀሳቀሱ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የወረቀት ጽሁፎቹም እየተሰራጩ ያለበትን አካባቢ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

ከአንድ አመት በላይ ባስቆጠሩ ጊዜያት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በባህርዳር እንዲሁም በጎንደር ከተሞች ጸረ-መንግስት መልዕከት ያላቸው ጽሁፎች ማንነታቸው ሊታወቅ ባልቻለ አካላት ሲበተኑ እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል።

ይህንኑ ድርጊት ያረጋገጡት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ፣ በሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ሆኖ የቆየው አለመረጋጋት ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ባለማግኘቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እንዳለበት ፓርላማውን ጠይቀዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም አዋጁ መራዘም እንዳለበት ለፓርላማ ባቀረበው ተመሳሳይ ማብራሪያ አሳስቧል።

ከሁለቱ መንግስታዊ አካላት የቀረበውን ማብራሪያ ያደመጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ መወሰኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ፓርላማው ኮማንድ ፖስቱ በድንበር አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሰፍንም ጠይቋል። የኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰንበት የድንበር አካባቢ ከሶስት ወር በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት ዕልባት አለማግኘቱን የተለያዩ አካላት ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በመንግስት የሚደገፉ የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ግድያና ዘረፋ ሲፈጽሙ እንደነበር በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መቶች ሊግ በበኩሉ ለወራት በዘለቀው በዚሁ ግጭት ከሁለቱ ወገኖች ከ400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በዚሁ ግጭት ዙሪያ የመከረው የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) በበኩሉ ለሰዎች ሞት ምክያት የሆነው ድርጊት ዕልባት እንዲያገኝና ግጭቱ ምርመራ እንዲካሄድበት ጥሪው ማቅረቡ ይታወሳል።

ኮማንድ ፖስቱ የቦታውን ስም ባይጠራም በድንበር አካባቢዎች ግጭት መኖራቸውን ለፓርላማው አረጋግጧል።

የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት በሁለቱ ክልሎች የቀጠለው ግጭት ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ቢያረጋግጡም ምን ያህል ሰው በአደጋው እንደሞተ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሃሙስ እንዲቀጥል ከመወሰኑ በፊት የመንግስት ባለስልጣናት ህዝቡ አዋጁ እንዲቀጥል ፍላጎት አሳይቷል በማለት መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ነው።

በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገውን ይህንኑ አዋጅ ተከትሎ ከ20ሺ በላይ ሰዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ወደ 5ሺ የሚጠጉት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ኮማንድ ፖስቱ ማክሰኞ ይፋ አድርጓል።

አለም ቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የተለያዩ ሃገራት አዋጁ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መባባስ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ቅሬታን ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል።