በኢትዮጵያ የተዘረጋው የአንድ ብሄር የበላይነት በአስቸኳይ መስተካከል ይኖርበታል ሲሉ የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ጥሪ አቀረቡ

ኢሳት (ጥቅምት 9 ፥ 2009)

በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በሃገሪቱ የዘረጋውን የአንድ ብሄር የበላይነት የፓለቲካ ስርዓት በአስቸኳይ ማስተካከል ይኖርበታል ሲሉ የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ጥሪ አቀረቡ።

ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የሶማሊላንድ ዲፕሎማት በተለያዩ ጊዜያት ከሃገሪቱ ጋር ለመምከር የሚመጡ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስቴር ሃላፊዎችን የአንድ ብሄር ብቻ ተወካይ መሆናቸውንና ጉዳዩ ጥያቄ እንዳሳደረባቸው መናገራቸውን ሶማሊላንድ ፕሬስ ጋዜጣ ዘግቧል።

ራሷን እንደ ነጻ ሃገር አድርጋ ባወጀችው ሶማሊላንድ ውስጥ ከሚታተመው ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስን ያደረጉት ዲፕሎማቶች መንግስት በዘረጋው የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የሌሎች ብሄረሰቦችን ማሳተፍና ስልጣንን ማጋራት እንደሚገባው ገልጸዋል።

የሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት የሚናገሩት ባለስልጣናቱ መወሰድ ይኖርበታል ያሉት የስልጣን ማጋራት ዕርምጃ በአፋጣን ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ለጋዜጣው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሶማሊላንድ ጋር በተለያዩ ጊዜያት የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነቶች እና ድርድሮች ቢያካሄዱም ለእነዚሁ ወሳኝ ድርድሮች ከኢትዮጵያ በኩል የአንድ ብሄር ተወካይ ብቻ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ባለስልጣት ለሶማሊላንድ ፕሬስ ተናግረዋል።

ከውጭ ጉዳይና ከመከላከያ ሚኒስትሮች በኩል ሁሌም ለድርድር ወደ ሶማሊላንድ የሚመጡ አመራሮች ለምን የአንድ ብሄር ብቻ ተወካይ ይደረጋሉ ሲሉ ዲፕሎማቶቹ ጥያቄን አቅርበዋል።

ሶማሊላንድ ራሷን እንደነጻ ሃገር አድርጋ ከ25 አመት በፊት ማወጇን ተከትሎ ኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነቷን በማጠናከር ቀዳሚ ሃገር መሆኗ ይነገራል።

የሁለቱ ወገኖች አመታዊ የንግድ ልውውጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን በከፊል እየተጠቀመች ትገኛለች። ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ጠንካራ ነው የተባለ ግንኙነት ቢኖራቸውም የሶማሊላንድ ባለስልጣናት እንዲህ ያለ ቅሬታን ሲያቀርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።

ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን በጋራ ለማልማት ከሶማሊላንድ ጋር ድርድር ስታካሄድ ቢቆይም ድርድሩ ውጤት ባለማምጣቱ ምክንያት አንድ የተባበሩት አረብ ኤመሬት ኩባንያ ወደቡን ሙሉ ለሙሉ ለማልማት ስምምነት መፈጸሙን መዘገባችን ይታወሳል።

ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ወደቡን የተረከበው ዲፒ ወርልድ (DP World) የተሰኘ ኩባንያ የራሱን የአገልግሎት ታሪፍ በማውጣት የወደቡ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።