በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የዜጎችን ህይወት አስጊ ደረጃ ላይ እንደጣለው ጎል ኢትዮጵያ አስታወቀ

ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ተከስቶ የማያውቅ ርሃብ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱንና ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በርሃብ መጠቃታቸውን ጎል ኢትዮጵያ የድርቁን ሰለባዎች በማነጋገር ጥናታዊ ሪፓርቱን አቅርቧል።

የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ወላጅ አልባ ሕጻናትን የሚያሳድጉ ወ/ሮ ዳኒስቶ የተባሉ በደቡብ ክልል ነዋሪ የደረሰባቸውን ሰቆቃ ሲናገሩ ”ባለቤቴን በድንገተኛ የሁለት ቀናት ሕመም በሞት ካጣሁ ስድስት ዓመት ሆኖኛል። ከባለቤቴ ሞት በኋላ አራቱን ልጆቼን መመገብ ተስኖኛል። የማበላቸው ነገር በማጣቴ ትልልቆቹን ልጆች ቢያንስ እየሰሩ እየበሉ መማር እንዲችሉ ብዬ ወደ ዘመዶቼ ሩቅ ቦታ ላኩዋቸው። እስካሁን ድረስ ከዓመት በላይ ዓይናቸውን አይቼውም አላውቅም።” ብለዋል።

በእርሻ ስራ ላይ በአነስተኛ ክፍያ ተቀጥረው የሚሰሩት ወ/ሮ ዳኒስቶ አክለውም ”እኔ ጋር አብረውኝ ያሉትንም ትንንሾቹን ልጆቼንም ለመመገብ አቅሙ የለኝም። እቤት ዓይናቸውን እያየሁ ይዣቸው ቁጭ እላለው። ባለፈው ዓመት ዝናብ ባለመጣሉ የእርሻ ምርት ቀንሷል። በዚህም ምክንያት ስራ ማግኘት አልቻልኩም። ይሄ አስቸጋሪ ወቅት ነው የሆነብኝ። ልጆቼና እኔ በጣም ይርበናል። ምናልባት ዝናቡ ዘንድሮ ከጣለ ስራ አገኝና ልጆቼንም በቂ ምግብ እመግባቸው ይሆናል። ልጆቼ ችግሬ ይገባቸዋል ቢሆንም እናት ነኝና እነሱን መርዳት አለብኝ።” ሲሉ ምሬታቸውን በእንባ በማጀብ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በርሃብ ምክንያት ሕጻናት ትምህርታቸውን እያቋረጡ መሆኑን ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው የታወቃል።