በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በህጻናት ላይ ከጦርነት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ጉዳት እያደረሰ ነው ተባለ

ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የድርቅ አደጋ በህጻናት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ እያደረሰ ካለው አደጋ ጋር ተመሳሳይ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቁ።

ይኸው በስድስት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ ከ 400ሺ በላይ በሚሆኑ ህጻናት ላይ ክፉኛ የአካልና የጤና ችግርን እያስከተለ እንደሚገኝ ድርጅቱ ገልጿል።

ድርቁ በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ጦርነት በሶሪያ ህጻናት ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

በኢትዮጵያ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋና በሶሪያ ቀጥሎ የሚገኘው ጦርነት በአለማችን ግንባር ቀደም የሰብዓዊ እርዳታን የሚፈልጉ አስቸኳይ ችግሮች ሆነው ተገኝተዋል ሲሉ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ካሮሊን ማይልስ ገልጸዋል።

ለዚሁ አፋጣኝ የነብስ አድን ስራም የህጻናት አድን ድርጅት ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚፈልግ ተወካዩ ይፋ ማድረጋቸውን ኒውስ 24 የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

ድርቁ ዱዳትን እያደረሰ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ዘገባን ያቀረበው አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ መግለጻቸውን አስነብቧል።

በድርቁ ሳቢያ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው እና የአስር ልጆች አባት የሆኑት ሞሃመድ ዱባሃላ ከነበራቸው 53 ላሞች መካከል አምስቱ ብቻ መትረፋቸውን ለቴለቪዥን ጣቢያው አስረድተዋል።

በተለይ ህጻናት ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ሃዘን እንደተሰማቸው የገለጹት አርብቶ አደሩ ከመንግስት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በድርቁ ሳቢያ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልና የድርቁ ጉዳትም እየከፋ እንደሚሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል።