(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 16/2010) በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ ሁኔታ ሰራዊቱን ሊጎትተው አይገባም ሲሉ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹሙ አሳሰቡ።
ኢታማጆር ሹሙ ጄኔራል ሰአረ መኮንን በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ ከዘራችን ይልቅ በኢትዮጵያዊነታችን እናስብ የሚል ነው በማለትም ተናግረዋል።
በፓርቲዎች ስኩቻ ውስጥ ግን አያገባንም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከሐገር መከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ጋር የተወያዩትና በመከላከያ ሰራዊቱ ፕሮግራም ላይ በተላለፈው መልዕክታቸው ሰራዊቱ ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ ለሕገመንግስቱና ለሕገመንግስታዊ ስርአቱ እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
በፖለቲካ ሁኔታዎች ልንጎተት አይገባም በማለት ያሳሰቡት ጄኔራል ሰአረ መኮንን የፓርቲዎ ሽኩቻና ልዩነት የራሳቸ ጉዳይ ነው እኛ ወደዚህ ከተሳብን የባለሙያ ተግባር አይሆንም ብለዋል።
ሰራዊቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን ከዘር አስተሳሰብም መራቅ ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ኢታማጆር ሹሙ ጄኔራል ሰአረ መኮንን “በዘር ማሰብ ከጀመርን የሕገመንግስቱ ጠባቂ ልንሆን አንችልም፣ሕዝቡን እርስ በርሱ እናባላዋለን” ሲሉ አሳስበዋል።
አሁን በሃገሪቱ የታየው ለውጥም በዘር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት እናስብ የሚል ነው በማለት ለውጡ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ መቃኘቱን ተናግረዋል።
በሰራዊቱ ውስጥ ከእንግዲህ የፓርቲ ልሳናት የሚነበቡት በባለስልጣናት ፍላጎት እንጂ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በሰራዊቱ መዋቅር የፓርቲ ልሳናት እንደማይቀርቡና እንደማያስፈልጉም ገልጸዋል።
በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የኢሕአዴግ የትንተና መጽሔቶችና ጋዜጦች በቋሚነት ሲቀርቡ መቆየታቸውንም የሰራዊቱ አባላት ሲናገሩ ቆይተዋል።
እንደ ጠቅላይ ኢትማዦር ሹሙ ጄኔራል ሰአረ መኮንን አባባል ከእንግዲህ የኢሕአዴግም ሆነ የሌላ ፓርቲ ልሳናት በሰራዊቱ ውስጥ በመመሪያ እንዲያነቡ የሚደረግበት ትዕዛዝ አይኖርም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ወደ 4ሺ ከሚጠጉ የመከላከያ ሰራዊት መኮንንኖች ጋር መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለመኮንኖቹ ሰራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በመሆን ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ማሳሰባቸው ተመልክቷል።