በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ስድስት ሚሊዮን በሚደርሱ ዜጎች ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ መጋረጡ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 30 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ በአራት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ስድስት ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሰዎች ለሰዎች የተባለው የጀርመኑ ግብረ ሰናይ ድርጅት አሳሰበ።

በሃገሪቱ ያለው ይኸው የከፋ የምግብ እጥረት በአለም መገናኛ ተቋም በቂ ሽፋንን እያገኘ እንዳልሆነ የገለጸው ድርጅቱ በተለይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና፣  ኬንያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች ድርቁ የከፋ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ለረጅም አመታት በሰብዓዊ ድጋፍ እና የልማት ስራዎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ሰዎች ለሰዎች የድርቅ አደጋ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሆነችባቸው ሃገራት ከኢትዮጵያ የበለጠ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋንን እያገኙ እንደሆነ አስታውቋል።

ችግሩ አፋጣኝ ርብርብ ካላገኘም 5.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከምግብ እጥረት የተነሳ ህይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ የጀርመኑ የሰብዓዊ ተቋም ሃላፊዎች ከጀርመን በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል።

አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ድርቁ ወደ ከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊሸጋገር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

“እርግጥ ነው በጎረቤት ሶማሊያ የከፋ የምግብ እጥረትና የሰዎች ሞት ማጋጠሙ ቢታወቅም፣ ኢትዮጵያ ችላ ልትባል የምትችል ሃገር አይደለችም” ሲሉ የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ የበላይ ሃላፊ የሆኑት ፒተር ሬነር ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸውን ሲያሳውቁ ቢቆዩም የጀርመኑ ግብረ ሰናይ ተቋም ቁጥሩ 5.7 ሚሊዮን መሆኑን አመልክቷል።

ከመዲናይቱ አዲስ አበባ በ500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የከፋ የምግብ እጥረት ተከስቶ እያለ በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋት ኣለመገኘቱ ያጋጠመ ነገር ያለ አይመስልም ሲሉ የድርጅቱ ሃላፊ ፒተር ሬነር ተናግረዋል።

ሃገሪቱ ባለፈው አመት ተከስቶ ከነበረው የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ሳታገግም ባለችበት ወቅት አዲስ ድርቅ ማጋጠሙ ችግሩን አባብሶት ይገኛል ሲሉ ሬነር ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። አለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በተለይ በሶማሌ ክልል ያለው የምግብና የውሃ እጥረት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ600ሺ በላይ የጎረቤት ሃገራት ስደተኞች በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠው እንደሚገኙም ሰዎች ለሰዎች በድርቁ ዙሪያ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

መንግስት በበኩሉ ድርቁ እየተባባሰ መምጣቱን አረጋግጦ ለተረጂዎች የምግብ አቅርቦት ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ የአለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት ሃገራት ለረሃብ ስጋት የሆነውን የድርቅ አደጋ ለመታደግ አለም አቀፍ የእርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመሩን ሃሙስ ይፋ አድርጓል።

ባንኩ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራቶች ሊካሄድ ባሰበው በዚሁ ዘመቻ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት እቅድ እንዳለው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና የመን ለረሃብ ስጋት የሆነ አስከፊ የድርቅ አደጋ ተጋርጦባቸው እንደሚገኝ የባንኩ ፕሬዚደንት ጂም ዮንግ ኪም ገልጸዋል።

የአለም ባንኩ በአለም አቀፍ የልማት ፕሮግራም ስር ለሃገሪቱ በሚሰጠው ልዩ ድጋፍ 770 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት በቅርቡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳነን እንደሚያስተላልፍ ፕሬዚደንቱ ይፋ አድርገዋል።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ባንኩ ላደረገው አስቸካይ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽን በመስጠት ርብርብ እንዲያደርግ የአለም ባንክ ፕሬዚደንት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።