በኢትዮጵያ የተከሰተው አለመረጋጋት በኢንቨስትመት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ተባለ

ኢሳት (መስከረም 30 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አለመረጋጋት በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንና ለውጭ ባለሃብቶች ስጋር መፍጠሩን አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ባለሙያዎች ገለጹ።

ይኸው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በኢትዮጵያ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በሚደረገው ጥረት ላይ ሁለገብ የሆኑ መሰናክሎች እንደፈጠረ ብሪታኒያ ለንደን ከተማ በሚገኘው ብሉምበርግ ኢንተሊጀንሲ አለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ማርክ ቦህሉንድ ለብሉምበርግ አስረድተዋል።

ባለፈው ሳምንት በቢሾፍቱ ከተማ የደረሰውን ዕልቂት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሂዱ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ድርጊት 11 ፋብሪካዎች መውደማቸው ይፋ ተደርጓል።

በሃገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለውጭ ባለሃብቶች ስጋት ማሳደሩን የተናገሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ማርክ ቦህሉንድ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች የጸጥታ ሁኔታው እስኪሻሻል ድረስ እንቅስቃሴያቸውን ለመግታት መገደዳቸውን ገልጸዋል።

በአንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑንት ጃሬድ ጀፍሪ (Jared Feffrey) በበኩላቸው መፍትሄን የሚፈልጉ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ለብሉምበርግ የዜና አውታር አስረድተዋል።

የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚፈጀው ጊዜ ኢትዮጵያን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ከመክተቱ በተጨማሪ በውጭ ባለሃብቶች አስቸጋሪ ሁኔታን እንደሚፈጥር NKC አፍሪካ ኢኮኖሚክስ በተባለ ተቋም ውስጥ የሚሰሩት ተወካይ አክለው ገልጸዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በውጭ ባለሃብቶች ላይ ካደረሰው ተፅዕኖ በተጨማሪ በሃገር ውስጥ የንግድ እንስቃሴ ላይም ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የሃገር ውስጥ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ይኸው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባትን የማያገኝ ከሆነ ለአመታት ያህል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስመዝግባለች የተባለችው ኢትዮጵያ፣ የከፋ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል አለም አቀፍ ባለሙያዎች በማሰባሰብ ላይ ናቸው።

በ25 አመት የስልጣን ቆይታው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ይገኛል ሲል የዘገበው ብሉምበርግ የዜና አውታር ለወራት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውን አክሎ አስነብቧል።