ኢሳት (ጥቅምት 23 ፥ 2009)
በኦሮሚያና አማራ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ተገለጸ። የውጭ ባለሃብቶች ከእንግዲህ መዋዕለ-ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ እንደሚቸገሩ የምስራቅ አፍሪካ አደጋዎች ላይ የሚሰራ አማካሪ ድርጅት ገልጿል።
አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት እንደሚቸገሩና ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የውጭ ባለሃብቶች በስራ ላይ ይቆዩ ወይም ደግሞ አገሪቷል ለቀው ለመውጣት ይወስኑ የታወቀ ነገር እንደሌለ ዋሽንግተን ፖስት ረቡዕ ባወጣው ዜና ዘግቧል።
ኢኮኖሚዋ በአብዛኛው በእርሻ ላይ የተመሰረተችው ኢትዮጵያ፣ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋት በጨርቃጨርቅ ፣ በአበባ እርሻና በቀላል ኢንዱስትሪዎች የሚሰማሩ የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ከፍተኛ ፍላጎት አላት።
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የተወሰኑትን የውጭ ባለሃብቶች ፋብሪካዎችና የአበባ እርሻዎች በተቆጡ ተቃዋሚዎች መውደማቸው ይታወሳል። አብዛኞቹ የውጭ ባለሃብቶች ፋብሪካዎችና እርሻዎች ከገበሬዎች በግድ በተወሰዱ መሬቶች ላይ የተገነቡ መሆናቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
የኮሚውኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የውጭ ባለሃብቶች ንብረቶችን ለመቆጣጠር ችለናል ቢሉም፣ መትረየስ እና ከባድ መሳርያ የታጠቁ የመንግስት ወታደሮች የውጭ ባለሃብቶች ንብረቶችን እየጠበቁ እንደሆነ ዋሽንግተን ፖስት ረቡዕ ባወጣው ጽሁፍ ገልጿል። ሆኖም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ቁርኝት የፈጠሩ የውጭ ባለሃብቶች፣ ንብረቶቻቸውና ፋብሪካዎቻቸው ሳይወድሙባቸው እንደቀሩ ገልጿል። የአካባቢው ሽማግሌዎች ንብረቱ የራሳችን ነው በማለት ከመቃጠል አደጋ እንዳዳኑት ዋሽንግተን ፖስት የእርሻ ባለሃብቶችን ባለቤቶች ዋቢ አድርጎ በዘገበው ዜና አስታውቋል።
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች የውጭ ባለሃብቶች ፋብሪካዎች ሙሉ መልኩ በተቆጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ በሚባል መውደማቸው ተገልጿል። ለምሳሌ ከኢሬቻ ፌስቲባል ከደረሰው ዕልቂት በኋላ የቤልጂየም Giving Tree Nursery እና አፍሪካ ጁስ ተብሎ የሚጠሩት የእርሻ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ተገልጸዋል። ሌሎች እንደ ማኬየልስ ግሩፕ የተባሉት በኢትዮጵያ ለመስራት ወይም ለቆ ለመውጣት አለመወሰናቸውን ዋሽንግተን ፖስት ባቀረበው ሰፊ ዘገባ አብራርቷል።
በእንግሊዝ አገር የምስራቅ አፍሪካ አደጋዎች አማካሪ የሆኑት ኤማ ጎርደን (Emma Gordon) እንደሚሉት አብዛኞቹ የውጭ ባለሃብቶች የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸው፣ መንግስት በመሳሪያ የተደገፈ የአፈና ተግባር ከመውሰድ ይልቅ ለችግሩ የተለየ መፍትሄ እንዲሰጥ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የህዝባዊ እምቢተኝነት አራማጆች በአፈናና በጉልበት ሊቆም የማይችል ጥያቄዎችን በማንሳታቸው ይህንን አስተሳሰባቸውን የሚቀይር መፍትሄ የኢትዮጵያ መንግስት እስካላመጣ ድረስ ችግሩ አይቀረፍም ሲሉ ኤማ ጎርዶን ተናግረዋል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ እንደሚቸገሩ ሃላፊዋ ለዋሽንግተን ፖስት አብራርተዋል።