ኢሳት (ሃምሌ 20 ፥ 2008)
ኢትዮጵያ ካላት 90 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑ ህዝቦቿ ወደ 23 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆነው የብልሃርዚያ በሽታ ህክምናን የሚፈልግ እንደሆነና የበሽታው ስርጭትም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የአለም ጤና ድርጅት አስታወቁ።
የብልሃርዚያ በሽታ በአለማችን ካልጠፋባቸው ጥቂት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር 14 ሚሊዮን ታብሌት ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ መጓጓዙን የአለም ጤና ድርጅትን ዋቢ በማድረግ አፍሪካ ኒውስ ማክሰኞ ዘግቧል።
መርክ በተሰኘ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኩባንያ የተለገሰው ይኸው መድሃኒት ስድስት ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ህጻናት ተማሪዎችን ለማከም እንዲረዳ የጤና ድርጅቱ ገልጿል።
የመድሃኒት ልገሳውን ያደረገው ተቋም በኢትዮጵያ ያለውን የብልሃርዚያ በሽታ ለመቆጣጠር መድሃኒት ብቻ ማቅረቡ መፍትሄ አለመሆኑን በመግለጽ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
በኩባንያው የኢትዮጵያና ሱዳን እንዲሁም ከሰሃራ በታች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገራት ተወካይ የሆኑት ቶክሪ አህመዲ ኢትዮጵያ ካላት ከ90 ሚሊዮን ህዝብ መካከል 23 ሚሊዮን የሚሆነው በዚህ በሽታ መያዙንና ህክምናን የሚፈልግ እንደሆነ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የበሽታው ስርጭት የሚታይባቸው የተወሰኑ ከሰሃራ በታች አፍሪካ ሃገራት በየአመቱ 200ሺ ሰዎች የሚሞቱ ሲሆን፣ የብልሃርዚያ በሽታ ንጽህናው ባልተጠበቀ ውሃ በሚፈጠር ተዋስያን የሚፈጠር ተላላፊ በሽታ መሆኑ ይነገራል።
ይኸው ተላላፊ በሽታ በኢትዮጵያ በተለይ የውሃ እጥረት ባላቸው አካባቢዎች በብዛት የሚታወቅ ሲሆን፣ ህጻናት ተማሪዎች በበሽታው ከሚጠቁ ሰዎች መካከል አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።
የበሽታውን ስርጭት ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ለበርካታ አመታት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም በሽታው አሁንም ድረስ የበርካታ ሰዎች የጤና ችግር ሆኖ መቀጠሉ የአለም ጤና ድርጅት ያመለክታል።
ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ብቻ 43 ሚሊዮን ታብሌት መድሃኒቶች በሽታውን ለመቆጣጠር ቢሰራጩም አሁንም ድረስ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ተጨማሪ ጥረት እንደሚያስፈልግ የመርክ ኩባንያ ተወካይ ቶክሪ አህመዲ አክለው ገልጸዋል።