ጥቅምት ፲፬ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አብዲፈታህ መሐመድ ሐሰን በተጠባባቂነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
አቶ አብዲ መሐመድ ከሥልጣናቸው የተነሱት በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በሚመለከት ኃላፊነታቸውን በብቃት ካለመወጣታቸው ጋር ተያይዞ እንደሆነ ሪፖርተር ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን ከብራሰልስ አዲስ አበባ እንደገባ በመንግስት ሚዲያ በተገለጸበት ወቅት ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ የሚታዩት አቶ አብዲ ከአቶ በረከት ስምዖን፣ ከአቶ ጁነዲን ሳዶና ከሌሎች የ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር ከሳምንት በፊት ከኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት በማስትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል።
አቶ አብዲ፤ባለፈው ረቡዕ ያለውጤት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የሰላም ድርድር ላይ መንግሥትን በመወከል የተላከው ቡድን አባል ነበሩ ፡፡
እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤ከዚሁ ያለውጤት ከተጠናቀቀው ድርድር በሁዋላ ፕሬዚዳንቱ በሀላፊነታቸው የቆዩት ለጥቂት ለቀናት ብቻ መሆኑ ፤በክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ዘንድ ፕሬዚዳንቱ የተወገዱት ከድርድሩ ጋር በተያያዘ ነው የሚል ግምት አሳድሯል።
አቶ አብዲ ወደ መካ ለሃጂና ኡምራ ጉዞ ዝግጅት እያደረጉ በነበረበት ጊዜ ወደ ፌዴራል መንግሥት የአስቸኳይ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው መዛወራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል ተብሏል።
በዚህም ምክንያት ጉዟቸውን ለመሰረዝ ሳይገደዱ እንዳልቀሩ የጠቀሱትምንጮች፣ የተሰጣቸው ኃላፊነት ግን ምን እንደሆነ አላብራሩም፡፡
ጉዳዩን በሚመለከት አቶ አብዲን በጽሕፈት ቤታቸውም ሆነ በግል ስልካቸው ለማነጋገር የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡
በቅርቡ በተደረገ ግምገማ ከፓርቲ ሥራ አስፈጻሚነታቸው የተወገዱት የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት አመራሩና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ከቀናት በፊት ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ አቶ ደመቀ መኮንን በማስታወቅ ለህክምና በሚል ወደ ታይላንድ ሊያደርጉት የነበረው በረራ በደህንነት ሀይሎች መሰረዙንና ከአገር እንዳይወጡ መታገዳቸውን ኢንዲያኝ ኦሽን መዘገቡ ይታወሳል።