የካቲት ፲፬ ( አሥራ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በፋሽሽት ኢጣሊያ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያዊያን የሚታሰቡበት የካቲት 12 ቀን በተቀዛቀዘ ሁኔታ እንዲከበር ከመደረጉም በላይ በሃውልቱ መታሰቢያ ላይ የህወሃት አርማ እንዲውለበለብ መደረጉ የከተማዋን ነዋሪዎች በእጅጉ አበሳጭቷል።
በድርጊቱ የተበሳጩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፣ “ድርጊቱ ነውር ነው” በማለት አስተያየታቸውን እየሰጡ ሲሆን፣ “ህወሃት ሆን ብሎ የጀግኖችን ሰማአታት ቀን ከራሱ ታጋዮች ጋር እኩል ለማድረግ ያደረገው ሙከራ በአርበኞቹ ላይ እንደመሳለቅ ይቆጠራል” ብለዋል። ተቃውሞው በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃንም ቀጥሎአል።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓም 30 ሺ ኢትዮጵያውያን በግራዚያኒ ወታደሮች በግፍ መጨፍጨፋቸው ይታወቃል። ጭፍጨፋው የተካሄደው የፋሽስት ሙሰሎኒ ወኪል በሆነው ሮዶልፎ ግራዚያኒ ላይ አብራሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች፣ ግራዚያኒን ለመግደል ያደረጉትን ሙከራ ተከትሎ ነው።