ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለዉን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የሀገሪቱ የምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ከ11.5 በመቶ ወደ 12.1 በመቶ ማሻቀቡን የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰኞ አስታወቀ።
ወተትና ፓስታን ጨምሮ በተለያዩ የምግብ ዉጤቶች ላይ በየእለቱ የዋጋ ጭማሪ እየተመዘገበ መምጣቱንም መንግስታዊ ተቋሙ በወርሃዊ ሪፖርቱ አመልክቷል።
በተለይ በስድስት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ የሚገኘዉ የድርቅ አደጋ በሀገሪቱ የምግብ ነክ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረግ ከባለፈዉ ወር 0.6 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማስመዝገቡን ድርጅቱ ገልጿል።
የሀገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትም በሁለት አሀዝ በመመዝገብ አስር በመቶ ሆኖ መገኘቱን ኤጀንሲዉ ካወጣዉ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለዉ የድርቅ አደጋና የዉጭ ምንዛሪ እጥረት የሀገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት እንዲንር እያደረጉት እንደሚገኝ የአለም ባንክና ሌሎች የገንዘብ ተቋማት ይገልጻሉ።
መንግስት በቅርቡ የ18 ቢሊዮን ብር ተጨማር በጀት ማጽደቁም የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት ሊያባብሰዉ እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሳስበዋል።
ባለፈዉ ወር ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጣሸቀጦች ላይ ተመዝግቦ የነበረዉ የ8.4 በመቶ የዋጋ ግሽበት በታሀሳስ ወር ወደ 7.7 በመቶ ዝቅ ማለቱን የማእከላዊ ሰታትስቲክስ ኤጀንሲ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ እያሻቀበ የመጣዉን የዋጋ ግሸበትና የዉጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቆጣጠር መንግስት አፋጣኝ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት የፋይናንስ ተቋማት ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።