በኢትዮጵያ የማላዊ ምክትል አምባሳደር ከገንዘብ ምዝበራ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2008)

አዲስ አበባ በሚገኘው የማላዊ ኢምባሲ ውስጥ ተፈጽሟል ከተባለ ከፍተኛ ገንዘብ ምዝበራ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ የሃገሪቱ ምክትል አምባሳደር በማላዊ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።

የማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሯ ዶረን ካፓንጋ በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ስለተባለው የገንዘብ ምዝበራ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ረቡዕ ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

በኢምባሲው የገባበት አልታወቀም ከተባለ ከሶስት ሚሊዮን ዶላር ጉዳይ ጋር በተገናኘ ምክትል አምባሳደሯና የኤምባሲው ዋና ጸሃፊ ከአዲስ አበባ ወደ ማላዊ እንዲዘዋወሩ መደረጉ ይታወቃል።

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የማላዊ ፖሊስም አምባሳደር ዶረን ካፓንጋን በቁጥጥር ስር በማዋል ከማላዊ እስከ ኢትዮጵያ የዘለቀ ምርመራ መጀመሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሁለቱ የማላዊ የዲፕሎማቲክ አባላት አዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ የሃገራቸውን ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ሲያባክኑ መቆየታቸውን የማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ለጋዜጠኖች አስረድተዋል።

በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ጠፍቷል የተባለው ከሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብም፣ በድህነቷ ለምትታወቀው ማላዊ ከፍተኛ ገንዘብ መሆኑን የማላዊ የፖለቲካ አመራሮች ገልጸዋል።

በአምባሳደሩ ላይ የሚካሄደው ምርመራም እንደተጠናቀቀም ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል እንደሚገለፅና አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ፖሊስ ማስታወቁን ኒያሳ ታይምስ የተሰኘ የማላዊ ጋዜጣ አስነብቧል።

የሃገሪቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ቶሚክ ኒያኡዴ በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመውን የገንዘብ ምዝበራ ተከትሎ ሃገራቸው በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ወደ 82 አካባቢ ዲፕሎማቶችንና ተወካዮችን ወደማላዊ በመጥራት ምክክር ማካሄድ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚበልጠው ገንዘብ በምን ሁኔታ ላይ እንደዋለ ለማወቅ የማላዊ መንግስት አዲስ አበባ ድረስ የዘለቀ ምርመራን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ ጉዳዩም በማላዊ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ መገኘቱን ለመረዳት ተችሏል።